የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የ2014/2015 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2015/2016 ዕቅድ ዝግጅት ዓመታዊ የሰራተኞች መድረክ ተካሄደ፡፡
ከየካቲት 27 እስከ መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ.ም ለ5 ተከታታይ ቀናት በተካሄደው መድረክ የመ/ቤቱ የኦዲትና የድጋፍ ዘርፍ የሥራ ክፍሎች የ2014/2015 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ተገምግሟል፡፡
ግምገማው አጠቃላይ የመ/ቤቱ ሠራተኞች በተገኙበት የተከናወነ ሲሆን ከውይይቱ በኋላም እያንዳንዱ የሥራ ክፍል ለ3 ተከታታይ ቀናት የ2015/2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አዘጋጅቶ በመጨረሻው ቀን መርሃግብር በመድረኩ አቅርበዋል፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በተገኙበት በዚህ የማጠቃለያ መድረክ የቀረበው ዕቅድ በመላው ሠራተኞች ውይይት ተደርጎበት የማሻሻያ ሀሳቦች ተወስደዋል፡፡
ስለዕቅዱ ግምገማም ሆነ ዝግጅት ከመድረኩ የተነሱ ሀሳቦች መሠረት በማድረግ የማጠቃለያ ሀሳብ የሰጡት ክብርት ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ የመ/ቤቱ የዕቅድ አፈጻጸም አካል የሆኑት የቋሚ ኮሚቴው አባላት በባለቤትነት ስሜት በመድረኩ በመገኘታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የመ/ቤቱን የ2014/2015 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም መሰረት አድርጎ በእያንዳንዱ የሥራ ክፍል የተዘጋጀው የ2015/2016 በጀት ዓመት ዕቅድ ተግባራዊ እንዲሆን የሁሉንም ሠራተኞች የጋራ ጥረት ይጠይቃልም ብለዋል፡፡
የመድረኩ ዓላማ በዕቅድና አፈጻጸም ላይ ያሉትን ጠንካራ ጎኖችና ክፍተቶች ለይቶ ለቀጣዩ ሥራ ለመዘጋጀትና ወጥ የሆነና ጥራት ያለው የኦዲት ተግባር ለመፈጸም መሆኑንም ዋና ኦዲተሯ ጠቁመዋል፡፡
ምክትል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ በበኩላቸው ለመ/ቤቱ ዕቅድ ትግበራ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችና ተገቢ ስልጠናዎች በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሠረት ይሟላሉ ብለዋል፡፡
ዕቅዱን ለማሳካት የሁሉንም ሠራተኞች ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን አክለው በመጥቀስም በመድረኩ የተነሱ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ በበኩላቸው ቋሚ ኮሚቴው የመ/ቤቱን ሥራ በኃላፊነት የሚቆጣጠርና የሚከታተል መሆኑን አስታውሰው መድረኩ መ/ቤቱ ምን አቅዶ እንደፈጸመና በአፈጻጸም ሂደት ያጋጠሙትን ዕንቅፋቶች መለየት ያስቻለ ነው ብለዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የዕቅድ አፈጻጸም እንዲሳካ እያደረገ ያለውን እገዛና ድጋፍ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ጨምረው የገለጹት ም/ሰብሳቢዋ መ/ቤቱ ቋሚ ኮሚቴው በኦዲት ተደራጊ ተቋማት ሀብት አጠቃቀም ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥርና ክትትል በተሳካ ሁኔታ ለማሳካት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሚና ግንባር ቀደም ነው ብለዋል፡፡
ሥራን በጥራትና በመልካም የሥነምግባር መርህ በታማኝነት መሥራት ከመ/ቤቱ የሚጠበቅ መሆኑን በመጥቀስም በመድረኩ የተካሄደው የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና ዝግጅት ትምህርት የሚወሰድበት ነው ብለዋል፡፡
የመ/ቤቱ ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና ዕቅድ ዝግጅት መላው ሠራተኞች በተገኙበትና ተሳትፎ በሚያደርጉበት ሂደት በየአመቱ የሚካሄድ ነው፡፡