News

የመ/ቤቱ አመራሮች የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የለውጥ ሥራዎችን እና የዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ግንባታዎችን ጎበኙ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ እና ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የለውጥ ሥራዎችን እና የዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ግንባታዎችን ጎበኙ፡፡

በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋናው መ/ቤት በነበረው የጉብኝት ቆይታ የተቋሙን ታሪካዊ ዳራ፣ በየዘመኑ የተሰሩ ሥራዎችና ተግዳሮቶች እንዲሁም ከመንግስት ለውጥ በኋላ ተቋሙ የሠራቸውን የለውጥ ሥራዎች የኮርፖሬሽኑ የዋና ስራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ይትባረክ መንግስቴ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ኃላፊው በገለጻቸው ኮርፖሬሽኑ ከሪፎርም በፊት በፋይናሽያል ኦዲት በየአመቱ አስተያየት ለመስጠት የማያስችል /disclaimer of Opinion/ የኦዲት አስተያየት ወጥቶ እንደማያውቅና በአሠራሩም በርካታ ችግሮች እንደነበሩበት በክዋኔ ኦዲት መታየቱን አስታውሰዋል፡፡

ከመንግስት ለውጥ በኋላ መ/ቤቱ ባደረገው የሪፎርም ሥራዎች ጠንካራ የመፈጸም አቅም መፍጠሩን፣ ገቢውን በእጅጉ ማሳደግ መቻሉን፣ ለሠራተኞቹም ምቹ የሥራ አከባቢ መፍጠሩን እና 10 አዳዲስ ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት ግንባታዎች ገንብቶ ማጠናቀቅ መቻሉን አብራርተዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅትም የራሱን ዋና መ/ቤት እና የፌዴራል የስነ-ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ህንጻዎች እድሳት ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ማከናወኑን አቶ ይትባረክ ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ኮርፖሬሽኑን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ በመሆን እና በኦዲት ሥራ እንደሚያውቁት አስታውሰው ከነበረበት ውስብስብ ችግር ወጥቶ በዚህ ደረጃ በአሠራሩ ተለውጦ በማየታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ የነበረበትን ችግሮች በመቅረፍ በተለይም ዘመናዊ የመኖሪያ መንደሮችን በፍጥነት እና በጥራት መገንባት የሚያስችል አቅም ላይ መድረሱ የሚያበረታታና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም በተለይ ዝቅተኛ የመክፈል አቅም ያላቸውን የመንግስት ሠራተኞች ታሳቢ ያደረጉ የመኖሪያ ቤት ግንባታዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ክብርት ዋና ኦዲተር እና ም/ዋና ኦዲተር በጉብኝታቸው የኮርፖሬሽኑን ዋና መ/ቤት፣ የፌዴራል የስነ-ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ህንጻ፣ የመካኒሳ፣ የቦሌ፣ የቀበና እና የገርጂ ዘመናዊ አፓርትመንቶች እና የመኖሪያ መንደሮች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *