News

የመሰረተ ልማት ተቋማት የተቀናጀ አሠራር ያለመኖር ከፍተኛ የሀብት ብክነት እያስከተለ ነው ተባለ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የቀድሞውን የፌዴራል የተቀናጀ መሰረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ የተቀናጀ የመሠረተ ልማት ግንባታ መስመር ዝርጋታና ሌሎች ተያያዥ አሠራሮችን አስመልክቶ በ2013/14 በጀት ዓመት በካሄደው የክዋኔ ኦዲት መሠረት በርካታ ክፍተቶች መታየታቸው ተገለጸ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም በኤጀንሲው ላይ የተሰራውን የኦዲት ሪፖርት መሠረት አድርጎ ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት አካሂዷል፡፡

ሀገራዊ የተቀናጀ መሰረተ ልማት መሪ ፕላን አለመዘጋጀቱ እና የመሰረተ ልማት የዕድገት አቅጣጫ የሚመራበት ማዕቀፍ የሌለው መሆኑ፣ የመሰረተ ልማት ግንባታና ዝርጋታዎች በተቀናጀ አሠራር ያለመሰራታቸውና በዚህም ከፍተኛ የሀብት ብክነት መከሰቱ በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ወቅት ተግባራዊ የሚደረገው የካሳ አከፋፈል ስርዓት፣ የመረጃ አያያዝና አደረጃጀት እና በሌሎች ተያያዥ አሠራሮች ላይ ክፍተቶች መኖራቸው ተነስቷል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ክቡር ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ የተነሱትን ነጥቦች አስመልክቶ በሰጡት ሰፋ ያለ ምላሽ በኦዲት ግኝቶቹ የተጠቀሱት ጉዳዮች ትክክለኛ መሆናቸውን ጠቅሰው በኦዲቱ የታዩ ችግሮችን ለመፍታት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትና በመድረኩ የተገኙ ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው ከቀረበው ማብራሪያ ምላሽ አኳያ ከዓመት በፊት በተመሳሳይ ኦዲት ግኝቶች ላይ የተሰጡ የኦዲት ማሻሻያ አስተያየቶች ተግባራዊነት ላይ የሚፈለገውን ያህል እርምጃ ያለመወሰዱን አንስተዋል፡፡

በተለይም በመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት መካከል ተገቢና የሚናበብ ቅንጅታዊ አሰራር ያለመኖሩ በሀገር ሀብት ላይ ከፍተኛ ብክነትና ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም በቅንጅታዊ አሠራር፣ በካሳ አከፋፈል ሥርዓት፣ በመመሪያና ደንብ አዘገጃጀትና ትግበራ፣ በመረጃ አያያዝና በሌሎችም ተያያዥ አሠራሮች ላይ ለከፍተኛ የህዝብ እሮሮ መነሻ የሆኑ ክፍተቶች በአፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጣቸው የቋሚ ኮሚቴው አባላት ጠይቀዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው ሚኒስቴር መ/ቤቱ ሀገራዊ በሆኑ መሰረተ ልማት ስራዎችን አቀናጅቶ መሥራት ላይ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን በማውሳት በኦዲቱ መሰረት በርካታ ክፍተቶች መታየታቸውን አንስተዋል፡፡

ችግሮቹን ለመፍታትም ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት የተደረገበትና የጸደቀ ስታንዳርድ ሊኖር እንደሚገባ የጠቆሙት ክብርት ዋና ኦዲተሯ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ምክክር የተደረገበት ሀገራዊ የመሰረተ ልማት መሪ ዕቀድ ሊኖር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ለመሰረተ ልማት በጀት ከመፈቀዱ በፊትም የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ዕቅድ መዘጋጀቱ ሊረጋገጥ፣ በመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት መካከል የተናበበና ቅንጅታዊ ስራ ሊኖር እና የካሳ ክፍያ ስርዓቱም ወጥና ወቅታዊ ሊሆን እንደሚገባ እንዲሁም የመሰረተ ልማት ዝርጋታና ግንባታዎች መረጃ የመመዝገብና የማስተዳደር ስራም መጠናከር እንዳለበት ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ አሳስበዋል፡፡

በውይይቱ መጨረሻ አስተያየታቸውን የሰጡት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስትያን ታደለ በበኩላቸው ከኦዲት ግኝቶቹ አንጻር ሚኒስቴር መ/ቤቱ ሀገራዊ መሰረተ ልማቶችን ተገቢ በሆነ መልኩ ከማስተባበር፣ ከማስተዳደርና ከመቆጣጠር አንጻር በመንግስት በአዋጅ የተሰጠውን ስልጣንና ኃላፊነት በሚገባ አለመወጣቱን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ተቋሙ ለኦዲት ግኝቶቹ ትኩረት በመስጠት እንዲሁም በመድረኩ የተሰጡ አስተያየቶችንና ማሳሰቢያዎችን መሰረት ያደረገ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ የድርጊት መርሀ ግብርና የአፈጻጸም ሪፖርት በአጭር ጊዜ ውስጥ አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በሚመለከቷቸው ጉዳዮች ዙሪያ አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር እንዲያደርጉ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

ለተጨማሪና ዝርዝር መረጃ፡- https://www.facebook.com/hoprparliament/videos/1585823855214843

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *