News

ወቅቱን የሚመጥን የኤሌክትሪክ እና የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ሥርዓት መገንባት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

የሀገሪቱን ቀጣይ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ትገበራ ፍላጎት እና ዓለም የደረሰበትን የቴክኖሎጂ እድገት የሚመጥን የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ሥርዓት መገንባት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የ2013/2014 በጀት ዓመት የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አፈጻጸምን አስመልክቶ ባካሄደው የክዋኔ ኦዲት በርካታ ክፍተቶች መታየታቸው በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከባለድርሻ አካላት ጋር ግንቦት 16 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው ይፋዊ የህዝብ ውይይት ተነስቷል፡፡

የኤሌክትሪክ እና የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድን በተመለከተ በህግ፣ በፖሊሲ፣ በደንብ እንዲሁም በአሠራር መስፈርቶች (standards) እና የትግበራ ስትራቴጂ አዘገጃጀትና አተገባበር ላይ ክፍተቶች መታየታቸው፣ በጥናት ላይ የተመሰረተ ዘላቂ ችግር ፈቺ አሠራር ያለመዘርጋቱ፣ ቆሻሻውን ለማስወገድ ፈቃድ ለሚወስዱ አካላት ስራ ከመጀመራቸው በፊት የአካባቢ ተጽዕኖን የሚመለከት ጥናት ቀድመው እንዲያቀርቡ የሚያስችል አስገዳጅ ሁኔታ ያለመኖሩ እና በዘርፉ ላይ ሁሉንም አካላት ማዕከል ያደረገ በቂ የስልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥርዓት ያለመዘርጋቱ ተጠቅሷል፡፡

በማስወገዱ ስራ ለተሰማሩ ተቋማት ሰራተኞች አስተማማኝ የደህንነትና የጤና ጥበቃ እርምጃን በተመለከተ እና በክትትልና ቁጥጥር ሥርዓቱም ላይ በቂ ስራ ያለመሰራቱ በመድረኩ ላይ የተነሳ ሲሆን የመረጃ አሰባሰብና አደረጃጀትን ጨምሮ የተናበበ የመረጃ ልውውጥን ከመፍጠር አንጻር ጉድለቶች መታየታቸው ተገልጿል፡፡

የባለስልጣን መ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ጌታሁን ጋረደው (ዶ.ር) እና ሌሎች የተቋሙ አመራሮች የኦዲት ግኝቶቹ አሠራሮቻቸውን ለመፈተሽና ለማሻሻል ዕድል የፈጠሩ መሆናቸውንና በግኝቶቹ መሠረት የማስተካከያ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አያይዘውም ቀደም ሲል ፖሊሲ ብቻ የነበረ መሆኑንና ከኦዲቱ በኋላ የዘርፉን የዓለም አቀፍ ልምድ መሠረት ያደረገና ሁሉንም የዘርፉን ስራዎች ያካተተ የአሠራር መስፈርት (standard) ተዘጋጅቶ በስራ ላይ መዋሉን ገልጸዋል፡፡

በቂ ባይሆንም ጥናት መካሄዱንና የግንዛቤ ማስጨበጫ የተወሰኑ ስራዎች መሰራታቸውን እንዲሁም ፈቃድ የተሰጣቸውን አካላት በመከታተልና በመቆጣጠር እስከማገድ የደረሰ እርምጃ መወሰዱን አክለው የገለጹት ኃላፊዎቹ በተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች እጅ ጭምር በርካታ የኤሌክትሪክ እና የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻ ክምችት መኖሩ የተለየ በመሆኑና በዘርፉ ላይ ያለው ግንዛቤም ዝቅተኛ በመሆኑ ጠንካራ የግንዛቤ ማስጨበጥና ሌሎች የአሠራር እርምጃዎች በቀጣይ ይተገበራሉ ብለዋል፡፡

የተቋማት አሠራር ዘላቂ በሆነ ህግና በስርዓት የሚመራ እንጂ ከአመራሮች መቀያየር ጋር መያያዝ እንደሌለበት በመጠቆም አስተያየታቸውን የሰጡት የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓቱ ውጤት ማሳየት ያለበት መሆኑንና በተለይም ተቋማትን ጨምሮ በየቦታው ካለው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ እና የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻ ክምችት አኳያ በቂ የግንዛቤ ማስጨበጥና የማስተዋወቅ ስራዎች እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡

በኦዲቱ ወቅት በተሰጡ ምላሾችና በመድረኩ በተሰጡ ማብራሪያዎች መካከል ያለመናበብ ክፍተት መኖሩን እና የቀረበው የኦዲት ማሻሻያ የድርጊት መርሀ ግብር ጥቅል መሆኑን በመጥቀስ አስተያየታቸውን የሰጡት ፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ በበኩላቸው በድርጊት መርሀ ግብሩ ቀን ተወስኖላቸው የታቀዱ በርካታ ተግባራት በምን ደረጃ ላይ እንደደረሱ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በሀገሪቱ አስከ 4,300 ቶን የሚደርስ የኤሌክትሪክ እና የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻ ክምችት መኖሩ ቀደም ሲል በተጠና ጥናት መረጋገጡን ጨምረው የገለጹት ም/ዋና ኦዲተሩ በዘርፉ ላይ ካለው ቆሻሻውን እንደ ሌላ ተራ ቆሻሻ እስከማየት የሚደርስ አነስተኛ ግንዛቤ አንጻር ተቋሙ ከፍተኛ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እንዲሰራና ለክትትልና ቁጥጥር ሥርዓቱም ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡

ኦዲቱ የዘርፉን ቀልጣፋነት፣ ወጪ ቆጣቢነትና አዋጭነት እንዲሆም ተገቢ በሆነ የአሠራር ስርዓት መመራቱንና ዘመናዊና ቀልጣፋ የመረጃ ቅብብሎሽ ስርዓት መኖሩን ትኩረት በማድረግ መካሄዱን ክብርት ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ አስተውሰዋል፡፡

አክለውም ኦዲቱ ትኩረት ባደረገባቸው በክትትልና ቁጥጥር፣ በመመሪያ አተገባበር፣ ቆሻሻውን ለሚያስወግዱ ሠራተኞች የደህንነትና የጤና ጥበቃ በማስጠበቅ፣ በዘመናዊ መረጃ አያያዝና ቅብብሎሽ፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሊደረግ በሚገባው ቅንጅታዊ አሠራር እንዲሁም ቆሻሻውን መልሶ በጥቅም ላይ በማዋል (Recycling) ረገድ ተቋሙ ሊያከናውናቸው የሚገቡ ተግባራትን በአግባቡ አለመፈጸሙን ክብርት ዋና ኦዲተር ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓታቸውን በማጠናከር እና የኦዲት ግኝቱን የእቅዳቸው አካል በማድረግ ሊሠሩ እንዲሁም የዘርፉ ስራ የሀገሪቱን ቀጣይ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ትግበራ ፍላጎት እና ዓለም የደረሰበትን የቴክኖሎጂ እድገት ታሳቢ ያደረገ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስትያን ታደለ በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት ባለስልጣን መ/ቤቱ የዛሬውን ትውልድ ፍላጎትና የመጪውን ትውልድ ምቹና ከአደጋ የተጠበቀ የስራ አካባቢ ከመፍጠር አንጻር ኃላፊነት ያለበት ተቋም መሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡

አክለውም የኦዲት ግኝቶቹን ለማስተካከል ቀጣይ ጥረቶች እንዲደረጉ በማሳሰብ ባለስልጣን መ/ቤቱ የተሻሻለና ከመድረኩ የተሰጡ አስተያየቶችን መሰረት ያደረገ አዲስ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ የድርጊት መርሀ ግብር በ10 ቀናት ውስጥ አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ እንዲሁም አፈጻጸሙንም በየ3 ወራት ሪፖርት እንዲያደርግ እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም በሚመለከቷቸው ጉዳዮች ዙሪያ የድርሻቸውን እንዲወጡ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *