የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የህዝብ ድምጽ እንደመሆኑ የሃሳብና የይዘት ብዝሃነት ያላቸው ፕሮግራሞች ተደራሽነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ተገለጸ፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሬዲዮና የቴሌቪዥን የዜናና ወቅታዊ ጉዳዮች አገልግሎት አሰጣጥ አፈጻጸም ውጤታማነትን በተመለከተ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2015/2016 የተከናወነ የክዋኔ ኦዲት ግኝት ላይ ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ አካሂዷል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በኦዲት ግኝቱ የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት ያላዘጋጀ መሆኑን፣ እንዲሁም የመንግስት ፖሊሲዎችን እና ህጎችን በኮርፖሬሽኑ ተግባራዊ መሆናቸውን የሚያረጋግጥበት እና የሃሳብና የይዘት ብዝሃነት ያላቸው ፕሮግራሞች ተቀርጸው ለህዝብ መቅረባቸውን የሚከታተልበት፣ በሚሰጠው አገልግሎት ህዝቡ ተጠቃሚ መሆኑን የሚገመግምበት፣ የተለያዩ አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶችና የህብረተሰብ ክፍሎች ሚዛናዊ የሆነ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ፍትሃዊ አገልግሎት ማግኘታቸውን የሚከታተልበት፣ በተለያዩ የሚዲያ ማሰራጫ መንገዶቹ የሚያስተላለፈውን የፕሮግራም ይዘት የሚገመግምበትና ስለሚያሻሽልበት ሁኔታ ሀሳብ የሚያቀርብበት እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች መከበራቸውን አጉልቶ የሚያሳይና የፖለቲካ ፓርቲዎችን በፍትሃዊነት የሚያገለግልበት እና ከአድማጭ ተመልካቾች በኮርፖሬሽኑ ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን የሚመረምርበትና ተገቢውን ውሳኔ የሚሰጥበት የአሠራር ሥርዓቶች ያልዘረጋ መሆኑን በመድረኩ ገምግሟል፡፡
በተያያዘም የኮርፖሬሽኑ ሥራ አመራር ቦርድ ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ ስብሰባ እንደማያደርግ፣ ኮርፖሬሽኑ የአርካይቭ ሀብትን ዲጅታላይዝ ከማድረግና የኦዲቶሪያል ፖሊሲውን ከመከለስ፣ ከማንኛውም አካል ነጻና ገለልተኛ ሆኖ ከመስራት፣ በቋንቋዎች ስርጭት ሽፋን፣ ከዜና ዘገባዎች እና ፕሮግራሞች የሥርጭት ጥራትና ተደራሽነት፣ ከቴክኖሎጂ እድገት አንጻር ክፍተቶች መኖራቸው በኦዲት ሪፖርቱ መጠቀሱ በቋሚ ኮሚቴው ተገልጾ የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ከኦዲት ግኝቱ በኋላ ክፍተቶችን ለማረም ያከናወኗቸውን የማሻሻያ ሥራዎች እዲያብራሩ ተጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰን ጨምሮ በመድረኩ የተገኙ የኮርፖሬሽኑ ሥራ አመራሮች የኦዲት ግኝቶቹን ትክክለኛነት አረጋግጠው ከኦዲት ሪፖርቱ በኋላ ፈጥነው ወደሥራ በመግባት በርካታ ውጤቶችን ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡
አመራሮቹ በሰጡት ሰፊ ምላሽና ማብራሪያ ከኦዲት ግኝቱ በኋላ ኢቢሲ ወደ ይዘት በሚል በርካታ የሪፎርም ሥራዎች ማከናወናቸውን፣ አለም አቀፍ የሚዲያ ኮምፕሌክስ በአዲስ አበባ እንዲሁም በተለያዩ ክልሎች ደረጃቸውን የጠበቁ ስቱዲዎችን መገንባታቸውንና ምቹ የሥራ አከባበቢ መፍጠራቸውን እንዲሁም የተለያዩ አዳዲስ ፎርማቶች ተቀርጸው ኢቢሲን የሃሳብ ቤት ለማድረግ እየሠሩ መሆኑን ገልጸው ነገር ግን በበጀት እጥረት ምክንያት መስራት ያለባቸውን ያህል ለማከናወን መቸገራቸውን አስረድተዋል፡፡
በየጊዜው የኮርፖሬሽኑ አሠራር እያደገ ቢመጣም ከይዘት፣ ከስርጭት፣ ከተደራሽነት፣ ከአድማጭ ተመልካቾች እርካታ፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ዜጎችን ከማገልገል አንጻር መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች ያሉ በመሆኑ በቀጣይ ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩበት እንደሚሆን የሥራ ኃላፊዎቹ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ተደሰ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ ለኦዲት ግኝት ትኩረት በመስጠትና በወቅቱ የድርጊት መርሃ ግብር በማዘጋጀት ግኝቶቹን ለማስተካከል ጥረቶችን መደረጋቸውን በጥሩ ጎኑ እንደሚያዩ ገልጸው የአሠራር መመሪያዎችን ከመተግበር፣ የሥራ አመራር ቦርዱ በየወቅቱ ተሰብስቦ ስራዎቹን ከመገምገም፣ ቅሬታዎችን ከማስተናገድ፣ ከአርካይቭ አያያዝ፣ ከቋንቋዎች ዜና ይዘት ስርጭትና በሌሎች በኦዲቱ በዝርዝር የተገለጹ ክፍተቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ ከኦዲት ግኝት በኋላ በ15 ቀን ጊዜ ውስጥ የድርጊት መርሃ-ግብር በማዘጋጀት ወደሥራ መግባታቸው ለኦዲት ግኝቶቹ የሰጡትን ትኩረት የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመው ኮርፖሬሽኑ በተለይም የህዝብ ድምጽ እንደመሆኑ የሃሳብና የይዘት ብዝሃነት ያላቸው ፕሮግራሞች ተደራሽነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
ክብርት ዋና ኦዲተሯ አያይዘውም ኮርፖሬሽኑ በፊት ከነበረበት በብዙ መንገድ ለውጥ እያስመዘገበ ቢሆንም የአሠራር ሥርዓቶችን ዘርግቶ ከመስራት፣ የመረጃ አያያዙን ዲጂታላይዝ ከማድረግ፣ የተለያዩ የመረጃ መንገዶችን ከማስፋትና ከማሳደግ እንዲሁም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መረጃዎች ተደራሽነት ከማሳደግ አንጻር ይበልጥ መስራት እና በአፍሪካም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ሰፊ ሽፋን ያለው ሚዲያ ለመሆን አቅዶ መስራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሪ ሞሲሳ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ ለኦዲት ግኝቶቹ የሰጠውን ትኩረት አጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው መሆኑን ገልጸው ከኦዲት ግኝቶቹ የበለጠ ሄዶ ተቋሙን አለም አቀፍ ተወዳዳሪ፣ ተደማጭና ተአማኒ ሚዲያ ለማድረግ መስራት አለበት ብለዋል፡፡
አያይዘውም ኮርፖሬሽኑ በመድረኩ የተሰጡ ግብዓቶችን መሠረት በማድረግ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ተግባራትን በመለየት አቅዶ እንዲሠራ እንዲሁም በየ3 ወሩ የኦዲት ግኝቶን ለማሻሻል የሚሰራውን ሥራ በተመለከተ ለቋሚ ኮሚቴውና ለሚመለከታቸው የኦዲት ባለድርሻ አካላት ሪፖርት እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡