የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአካባቢ፣ ደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በኦዲት ለተገኙበት ድክመቶች ትኩረት በመስጠት መስራት እንዳለበት አሳሰበ፡፡
የአካባቢ፣ ደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ከ2009 እስከ 2011 በጀት አመት የአየር ንብረት ለውጥን ለማሻሻል እና ለማጣጣም የተመደበውን ሀብት አጠቃቀም እና ለአየር ንብረት ለውጥ ትግበራ ለፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የሚያደርገውን ድጋፍ በተመለከተ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተካሄደው የክዋኔ ኦዲት ላይ ቋሚ ኮሚቴው ታህሳስ 16፣ 2013 ዓ.ም ህዝባዊ ይፋዊ ስብሰባ አካሂዷል፡፡
በስብሰባው ወቅት ኮሚሽኑን አስመልክቶ ከተነሱት የኦዲት ግኝቶች መካከል
- በዘላቂ ልማት ግቦች ላይ የሚተገበሩ ስራዎች የ15 ዓመት እቅድ አለማቀዱ፣ ለፈጻሚ አካላት አለማስተዋወቁና አለማሰራጨቱ፣
- የአየር ንብረት ለውጥ እቅድን ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስፈልጉ የገንዘብ ማፈላለጊያ ረቂቅ ፍኖተ ካርታ እ.ኤ.አ በ2017 ቢያዘጋጅም እ.ኤ.አ እስከ ማርች 2020 ድረስ በሚመለከታቸው አካላት አስተያየት ያልተሰጠበትና ያልጸደቀ መሆኑ፣
- በዘላቂ ልማት ግቦች የተመለከቱትንና ሌሎች በሀገሪቱ አየር ንብረት ለውጥ ላይ ያሉ ስጋቶችን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ አለመለየቱና የማጣጣሚያ መርሀግብር ያልተዘጋጀላቸው መሆኑ፣
- ሙቀት አማቂ ጋዞች ቅነሳ ግቦች፣ ውጤቶች፣ የልኬት እና የዘገባ አቀራረብ እንዲሁም ማረጋገጫ አገራዊ ማዕቀፍ ሊዘረጋና ተግባራዊ መደረጉን መከታተል ቢገባውም በተወሰኑ ክልሎች የሙቀት አማቂ ጋዞች ልኬት ያለበትን ደረጃ ለማወቅ ከተደረገ አነስተኛ ዳሰሳ ውጪ እንደ ሀገር በዘርፍ ጋዞቹን ለመቀነስ የታቀዱ ተግባራት አለመፈጸማቸው፣
- በስሩ የሚተገብራቸው ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እና በጀት መፈጸማቸውን ክትትል የሚደያርግበት ስርአት ዘርግቶ በአመታዊ እቅድ እየያዘ ተግባራዊ ማድረግ ቢገባውም በኦዲቱ የታዩ ፕሮጀክቶች ግን ይህንን የመንግስት አሰራር እየተከተሉ አለመሆናቸው፣
- የአየር ንብረት ለውጥን ለማሻሻልና ለማጣጣም በመተግበር ላይ ያሉ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ሪፖርት በየሩብ አመቱ አለመገምገሙ፣ ፕሮጀክቶቹ በመሬት ምን እንደሚመስሉ እየተገመገሙ አለመሆኑ፣ በባለሙያዎች በአግባቡ ክትትል የማይደረግ መሆኑና ክትትል በተደረገባቸውም ላይ የተገኙ ክፍተቶች እየተስተካከሉ ስለመሆኑ የተሰራው ስራ እዚህ ግባ የማይባል መሆኑ፣
- የዘርፍ መ/ቤቶች የአየር ንብረት ለውጥ ትግበራ ወቅት የገጠማቸውን ችግሮች ለይተው የሚያቀርቡበትና መፍትሄ የሚያገኙበት የአሰራር ስርአት አለመዘርጋቱ፣
- የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ያለው የቅንጅት ስራ ክፍተት ያለበት መሆኑ ይገኙበታል፡፡
የአካባቢ፣ ደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነና ምክትል ኮሚሽነሩ አቶ ከበደ ይገዙ ለቀረቡት ጥያቄዎች በዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ኃላፊዎቹ ኦዲቱ ተቋሙ አሰራሮችን ለማስተካከል እንዲነቃቃ ማድረጉን ጠቅሰው በኦዲት ወቅት በተገኙ አንዳንድ ግኝቶች ላይ የተሰሩ ስራዎችን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም ሃብት የሚለግሱ ሀገሮችና ድርጅቶች እንዲሁም ሀብት ለመለገስ የሚጠይቁትን መስፈርት የመለየት ስራ መሰራቱን፣ በእያንዳንዱ ወረዳ ያለው የመሬት መራቆት፣ የመራቆት ደረጃ እና መፍትሔ በጥናት መለየቱን እንዲሁም የፕሮጀክቶች አፈፃፀም የሚገመገምበት ስርዓት የተዘረጋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥን ለማሻሻል ያለው ችግር በኮሚሽኑ ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ የሁሉንም አካላት ትብብር ይጠይቃል ያሉት ኃላፊዎቹ በፌዴራል ያለውን መዋቅር በክልሎች እስከታችኛው እርከን ድረስ ለማውረድ ችግር መኖሩን እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት የተደረገው ጥረት ውስንነት ያለበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በመ/ቤቱ ኃላፊዎች ለኦዲት ግኝቱ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛና የተሰጠው ምላሽም በቂ አለመሆኑን በአፅንዖት አንስተዋል፡፡
የፌዴራል ዋናው ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ኦዲቱን ጠቃሚ ነው ብሎ በመውሰድ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት መስራት እንዳለበት ገልጸው ለዚህም ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ እቅድ በማዘጋጀት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፋይናንሻል ኦዲት ንዑስ ዘርፍ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙን በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት ኮሚሽኑ በኦዲት ለተገኙ ችግሮች በቂ ምላሽ አለመስጠቱን ጠቅሰዋል፡፡ የተከበሩ ወ/ሮ ሶፊያ የኮሚሽኑ አመራር ኦዲቱን መሰረት ባደረገ መልኩ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራትና ችግሩን ለመፍታት ስራዎችን ማሻሻል ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ በማያያዝም በመ/ቤቱ የውስጥ ኦዲትን በማጠናከርና የአማካሪነት ሚናውን እንዲወጣ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡