የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2015/2016 ኦዲት አመት በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የ2015 በጀት አመት የፋይናንስና ሌሎች አሠራሮች ላይ ባካሄደው የሂሳብ እና የክዋኔ ኦዲት መሠረት የታዩ ጉልህ የአሠራርና አገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶች በኦዲቱ በመታየታቸው የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ፡፡
ህዳር 18 ቀን 2017 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በሁለት ክፍለ ጊዜያቶች ተከፍሎ በሂሳብና በክዋኔ ኦዲት ግኝቶች ላይ በተካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት በአገልግሎት አሰጣጥ ፖሊሲና የአስራር ስታንዳርድ ዝግጅትና ትግበራ፣ በሰው ሀብትና የስራ አካባቢ መዋቅራዊ አደረጃጀት ሁኔታዎች፣ በኦንላይንና ዲጂታላይዝ አሠራር፣ የጸደቀ መመሪያን ባልተከተለ የገቢ አሰባሰብና አያያዝ፣ በሠራተኞች ስነ ምግባርና ተጠያቂነት፣በግዥ ስርዓት፣ በግንዛቤ አሠጣጥ፣ በዘመናዊ መረጃ አያያዝና ቅንጅታዊ አሠራር እንዲሁም በሌሎች አሠራሮች ላይ ክፍተቶች መኖራቸው በተደረገው የክዋኔ ኦዲት መረጋገጡ በመድረኩ ተነስቷል፡፡
ከዚህም ሌላ በ2015 በጀት አመት በተቋሙ የሂሳብ አሠራር ላይ ከተገቢ የሂሳብ አርዕስት ውጪ የተመዘገበ ከብር 11.7 ሚሊዮን በላይ መገኘቱ፣ ከብር 89.3 ሚሊዮን በላይ በሆነ ገንዘብ መመሪያን ያልተከተለና ያለውድድር ቀጥታ ግዥ እንዲሁም ከኤሌክትሮኒክስ የመንግስት ግዥ(EGP) ስርዓት ውጪ በመደበኛ አሠራር የቴክኖሎጂ ዕቃዎች ግዥ መፈጸሙ፣ ከብር 5. 9 ሚሊዮን በላይ በወቅቱ ያልተወራረደ ውዝፍ ተሰብሳቢ እና ከብር 1.2 ሚሊዮን በላይ ተከፋይ ሂሳብ መገኘቱ እንዲሁም በድምሩ ከብር 4.5 ሚሊዮን በላይ በጀት በስራ ላይ ያለመዋሉን ጨምሮ የጥሬ ገንዘብ ጉድለትና ሌሎች የሂሳብ አሠራር ክፍተቶች መታየታቸው በመድረኩ ተጠቅሷል፡፡
በግኝቶቹ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥ ከመድረኩ ተጠይቆ በስፍራው የተገኙ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አመራሮች የኦዲት ግኝቶቹ ትክክለኛ መሆናቸውን በመጥቀስና በኦዲቱ የታዩ ግኝቶችን ጨምሮ ቀደም ሲል የነበረውን የአገልግሎት መ/ቤቱን ብልሹ አሠራሮች ለመቅረፍ የሚያስችል ባለ አስራ አንድ አጀንዳ ሪፎርም እየተካሄደ መሆኑን በመጠቆም ጥረት እየተደረገበት ያለው የኢ-ፓስፖርት ቴክኖሎጂ ሙሉ ለሙሉ ሲተገበር ችግሮቹ የሚፈቱ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
የተቋሙን አመራሮች ምላሾች ተከትሎ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የአገልግሎት መ/ቤቱ ተቀባይነት በሚያሳጣ የኦዲት አስተያየት ውስጥ የሚገኝ እንዲሁም በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚማረሩበትና ቅሬታ የሚቀርብበት ተቋም መሆኑን ጠቅሰው የተጀመረውን ሪፎርም በማጠናከር የአገልግሎት አሠጣጥ ሥርዓቱን የበለጠ ማሻሻልና በአሉታዊ የሚነሳ የተቋሙን ስም መቀየር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሠ የክዋኔ ኦዲት ግኝቶቹን መሠረት በማድረግ በፖሊሲና ስታንዳርድ ዝግጅትና ትግበራ፣ በመዋቅራዊ አደረጃጀት፣ በአገልግሎት መስጫ ቦታዎች ምቹነት፣ በሠራተኞች ስነ ምግባር፣ በቴክኖሎጂ ትግበራ፣ በግዥ ስርዓትና በሌሎች አሠራሮች ላይ የታዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ተቋሙ ጥረት እንዲያደርግ ጠይቀው በተለይም በሀላፊዎች ልዩ ትዕዛዝ ህጋዊ መስፈርቶች ሳይሟሉ የሚፈጸም የፓስፖርት አሰጣጥ ህጋዊ ባለመሆኑ መቆም እንዳለበት በማሳሰብ ተቋሙ በሚዲያ በመታገዝ ለተገልጋዮች ግንዛቤ የመስጠት አሠራሩንም ማጠናከር ይገባዋል ብለዋል፡፡
በሂሳብ አሠራር ላይ የታዩ ክፍተቶችን በተመለከተም በተለይ ለተከሰተው የጥሬ ገንዘብ ጉድለት የውስጥ ኦዲት አሠራሩንና የቁጥጥር ስርዓቱን ክፍተት በመጠቆም ተጨማሪ አስተያየት የሰጡት ክቡር ም/ዋና ኦዲተር አቶ አበራ ታደሠ ያለአግባብ የተፈጸሙ የጥቅማጥቅም ክፍያዎች፣ ማረጋገጫ መነሻ ሰነድ ያልቀረበባቸው ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳቦች፣ በታቀደለት ጊዜ በስራ ላይ ያልዋለ በጀት፣መመሪያን ያልተከተሉ ግዥዎችና ሌሎች ግኘቶች የተቋሙ መሠረታዊ የፋይናንስ ስርዓት ችግሮች በመሆናቸው እንዲታረሙ ጠይቀው የማሻሻያ እርምጃ ተወስዶባቸዋል የተባሉ ግኘቶች በቀጣይ የክትትል ኦዲት የሚረጋገጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው የኦዲቱን ዋነኛ የትኩረት ጉዳዮች በመዘርዘር በክዋኔ ኦዲት ግኘቶቹ ላይ በሰጡት አስተያየት ያልተዘረጉ ተገቢ የአሠራር ሥርዓቶች መኖራቸው ለክፍተቶቹ መነሻ መሆናቸውን ጠቅሰው በህጋዊ አካል መጽደቅ የሚገባውን የአሠራር መመሪያ በማኔጅመንት አጽድቆ መተግበር ህጋዊ ያለመሆኑን እና የሰው ኃይል መዋቅራዊ ሁኔታና የስራ መዘርዝር ሳይስተካከል የሚተገበር ስራም ለብልሹ አሠራር የሚያጋልጥ ነው ብለዋል፡፡
የተቋሙ የስራ ባህሪ ለሙስናና ብልሹ አሠራር የሚያጋልጥ በመሆኑ የተጀመረው የሪፎርም ስራ መጠናከር ያለበት መሆኑን ጨምረው የጠቀሱት ክብርት ዋና ኦዲተሯ ህግን ያልተከተለ የገቢ አሰባሰብ፣ ከመመሪያ ውጪ የሆነና በሚመለከተው ህጋዊ አካል ሳይፈቀድ የሚከፈል የትርፍ ሰዓት ክፍያ ህገወጥ አሠራር መሆኑን ገልጸው የኢ-ፓስፖርት አሠራርን በማጠናከር፣ ለሁሉም ተገልጋይ እኩል የሆነ መስፈርትንና ህግን የተከተለ የፓስፖርት አሠጣጥን በመተግበር፣ የመንግስት የግዥ ሥርዓትን በመከተል፣የአገልግሎት መስጫ ቅርንጫፎችን በማስፋፋት፣የኦን ላይንና የዲጂታል አሠራርን በማጠናከር፣ የቅንጅታዊ አሠራርንና የመረጃ አያያዝ ሥርዓቱን በማዘመን እና ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተገልጋዮች አመቺ ሁኔታን በመፍጠር የተገልጋዩን እንግልት መቅረፍ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የሂሳብ ኦዲት ግኝቶቹን በማንሳት ተጨማሪ የማሻሻያ አስተያየቶችን የሰጡት ክብርት ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ የጎደለው የመንግስት ጥሬ ገንዘብ እንዲመለስ አሳስበው ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳቦች የሚመዘገቡት በቅድሚያ ከማን እንደሚሰበሰቡና ለማን እንደሚከፈሉ ሲታወቅ በመሆኑ ይህንን የሚገልጹ ሰነዶች መቅረብ አለባቸው ብለዋል፡፡
ለሶስተኛ ወገን የሚተላለፉ የአገልግሎት ግዠዎች አዋጭነታቸው ተጠንቶና የግዥ መመሪያን ተከትለው መሆን እንዳለባቸው ጨምረው የጠቀሱት ክብርት ዋና ኦዲተሯ በኤሌክትሮኒክስ የመንግስት ግዥ ስርዓት ያልተመዘገቡ አቅራቢዎች በሌሎችም አካባቢዎች የሚታዩ በመሆናቸው ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግስት ተቋም በዚህ የግዥ ሥርዓት ላይ የተጠናከረ አሠራር እንዲፈጥር ም/ቤቱ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ የሺመቤት ደምሴ (ዶ/ር)በሁለቱም የውይይት መድረክ ክፍለ ጊዜያቶች በሰጧቸው ዝርዝር የማጠቃለያ አስተያየቶች በአገልግሎት መ/ቤቱ ላይ የታዩ የሂሳብም ሆነ የክዋኔ ኦዲት ግኝቶች ተቋማዊ መሠረታዊ የአሠራር ክፍተቶችን ያሳዩ መሆናቸውን ጠቅሰው ያልተስተካከሉ አሠራሮችን በማረም፣ ተገቢ የኦዲት ግኝት ማስተካከያ እርምጃዎችን በመውሰድና የተጀመረውን የሪፎርም ስራ በማጠናከር ተቋሙ አሰራሩን አሻሽሎ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአፈጻጸም ሪፖርቱን እንዲያቀርብ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡