News

ከተቋማትና ግለሰቦች ፍላጎት በላይ የአሠራር ህጎችና መመሪያዎች መከበር እንዳለባቸው ተገለጸ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በጂንካ ዩኒቨርሲቲ የ2013 በጀት ዓመት የፋይናንስ አሠራርና ንብረት አስተዳደር አፈጻጸም ላይ ባካሄደው የሂሳብ ህጋዊነት ኦዲት መሰረት በርካታ የህግና መመሪያ ጥሰቶች መታየታቸው ተገለጸ ፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ግንቦት 9 ቀን 2015 ዓ.ም ከዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር ህዝባዊ ውይይት አካሂዷል፡፡

በመድረኩ እንደተገለፀው በዩኒቨርሲቲው ከብር 13.4 ሚሊዮን በላይ የግዥ መመሪያን ያልተከተሉ ግዥዎች መፈጸማቸው፣ ከብር 7.9 ሚሊዮን በላይ በወቅቱ ያልተሰበሰበ ሂሳብ መገኘቱ እና ሌሎች የተሰበሰበ ግብርን ለሚመለከተው አካል ገቢ ያለማድረግ፣ ደንብና መመሪያን የጣሰ የአበል ክፍያ መክፈል፣ በውስጥ ገቢ መሸፈን የሚገባቸውን ወጪዎች ከመደበኛ በጀት መጠቀም እና ህግና መመሪያን የጣሱ የጨረታ ሂደቶች መከናወናቸው በኦዲቱ ታይቷል፡፡

በተማሪዎች ምግብ ቤት ግምጃ ቤት እና በቤተ መጻህፍት አሠራር እንዲሁም በተሽከርካሪዎች አያያዝና አጠቃቀም የታዩትን ጨምሮ በርካታ የንብረት አስተዳደር፣ አያያዝ፣ አጠቃቀምና አወጋገድ ጉድለቶች በኦዲቱ መገኘታቸውም በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡

የኦዲት ግኝቶቹን አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት የዩኒቨርሲቲው አመራሮች የተጠቀሱት የኦዲት ግኝቶች ትክክለኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዚዳንት ዶ.ር ኩሴ ጉዲሼ ጎሮያን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች በሰጡት ምላሽ የሠራተኞች እጥረት እና የአቅም ክፍተት መኖር ለችግሮቹ መከሰት ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰው አንዳንድ ወቅታዊ የዩኒቨርሲቲው ተጨባጭ ሁኔታዎች በግዥ፣ በጨረታና በሌሎች አሠራሮች ላይ ህግና መመሪያን ለመከተል እንዳላስቻሏቸው እና የኦዲት ግኝቶችን ለመቅረፍም በጥረት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲው አብዛኞቹ ችግሮች መነሻ በእቅድ ያለመመራትና ከአሠራር ህግና መመሪያ በላይ ለተቋምና ለግለሰቦች ፍላጎት ቅድሚያ የመስጠት አሠራር መሆኑን ጠቁመው የቱንም ያህል የማያሰሩ ሁኔታዎች ቢኖሩ ህግና መመሪያዎች ሳይጣሱ ከሚመለከታቸው ህጋዊ አካላት ጋር በመምከር የአሠራር ችግሮችን መፍታት ይገባ ነበር ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለሙስናና ብልሹ አሠራር ሊያጋልጡ የሚችሉ በርካታ አሠራሮች ያሉበት መሆኑን የስነምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ባደረገው ጥናት የተረጋገጠ መሆኑ በመድረኩ ላይ የተነሳ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው ብልሹ አሠራሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ የመጡበት ሁኔታ በመኖሩ አሠራሮችን በመፈተሽ፣ የአመራር እና የባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ እና የውስጥ ኦዲተሮችን አቅምና ሚና በማጎልበት ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው በ2014 በጀት ዓመት በዩኒቨርሲቲው ላይ በድጋሜ በተደረገው ኦዲት መሰረት የተወሰኑ ግኝቶች መስተካከላቸውን ጠቅሰው በተለይም በተሰብሳቢ ሂሳብ፣ በግዥ ሥርዓትና በንብረት አስተዳደር፣ አያያዝና አጠቃቀም ረገድ ያሉ ችግሮች አሁንም ድረስ የቀጠሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ያለአግባብ የተከፈሉ የአበልና ሌሎች ክፍያዎች ተመላሽ እንዲደረጉና ከአሠራር ውጪ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ክፍያውን የፈጸሙ አካላትም በህግ እንዲጠየቁ ያሳሰቡት ክብርት ዋና ኦዲተሯ ከውስጥ ገቢ መጠቀም ሲገባ ከመደበኛ በጀት ወጪ የተደረገ የመንግስት ገንዘብ እንዲመልስ እና ህጋዊ የቴክኒክና የዋጋ ማወዳደሪያ ሂደቶችን የጠበቁ የጨረታ አሠራሮች እንዲተገበሩም አሳስበዋል፡፡

ቀደም ሲል የታዩ የኦዲት ግኝቶችን በማስተካከል ረገድ ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቀውን ያህል ያለመስራቱን የጠቀሱት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስትያን ታደለ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ትውልድ እንዲቀርጽና ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዲያፈራ አደራ የተሰጠው የትምህርት ተቋም እንደመሆኑ ህግና መመሪያን የጣሱ አሠራሮችን ማሳየቱ ትልቅ ክፍተት ነው ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ተቋም እንደመሆኑ የሠራተኞቹን አቅም መገንባት እንደሚገባውና ሌሎች ችግሮችን ማስተካከል እንደሚኖርበት ማሳሰቢያ የሰጡት ሰብሳቢው የግኝት ማስተካከያ የድርጊት መርሀ ግብር በ10 ቀናት ውስጥ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በሚመለከታቸው የተቋሙ ጉዳዮች ዙሪያ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ አቀጥጫ ሰጥተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *