የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት የመድሃኒት አቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደር ላይ በ2015/ 2016 ኦዲት ዓመት ባካሄደው የክዋኔ ኦዲት መሠረት የታዩ የአሠራር ክፍተቶችን ለማስተካከል እየተወሰዱ ያሉ አበረታች ጥረቶች እንዲጠናከሩ ታህሳስ 23 ቀን 2017 ዓ.ም በተካሄደው ህዝባዊ ይፋዊ የውይይት መድረክ ተጠየቀ፡፡
የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የኦዲት ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት መድረክ በዝርዝር እንደተገለጸው አገልግሎት መ/ቤቱ በመድሃኒት ግዥ እቅድና ትግበራ፣ በግዥ መመሪያ አዘገጃጀት እና በመንግስት ግዥ መመሪያ አተገባበር፣ በአመታዊ ቆጠራ አተገባበር፣ በዱቤ ሂሳብ አሰባሰብ፣ በሚያገለግሉና በማያገለግሉ መድሃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎች ልየታና አያያዝ፣ በመረጃና ማስረጃ አደረጃጀትና አያያዝ እንዲሁም በመድሃኒት ጥራት ቁጥጥር፣ በማከማቻ መጋዘኖች ምቹነትና በመድሃኒቶች አያያዝና አጠባበቅ እንዲሁም በሌሎች የመድሃኒትና የህክምና ግብአቶች አያያዝ፣ አቅርቦትና ስርጭት ረገድ ጉልህ ጉድለቶች ታይተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አብድርቃድር ገልገሎ (ዶ.ር) ጨምሮ በመድረኩ የተገኙ የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት አመራሮች የግኝቶቹን ትክክለኛነት በማረጋገጥና ግኝቶቹ ለተቋሙ አገልግሎት አሠጣጥ መሻሻል ጠቃሚ ግብአቶች የተገኙባቸው መሆኑን በመጥቀስ በግኝቶቹና እየተወሰዱ ባሉ የማስተካከያ እርምጃዎች ዙሪያ ዝርዝር ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ይህንኑ ተከትሎ የቋሚ ኮሚቴው አባላት አገልግሎት መ/ቤቱ ግኝቶቹን ለማስተካከል እየወሰዳቸው ስላሉ አበረታች እርምጃዎች አመስግነው በአገልገሎት መ/ቤቱ አሠራር ዙሪያ ለተገልጋዮች ግንዛቤ የማስጨበጥ ተግባራትን ጨምሮ በቀሪዎቹ ግኝቶች ላይ ቀጣይ የተጠናከሩ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አሳስበዋል፡፡
በይፋዊ የውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስቴር የሀብት፣ የአስተዳደርና የቁጥጥር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ በበኩላቸው የኦዲት ግኝቶቹ ትክክለኛና ተገቢ መሆናቸውን በማንሳት በሰጡት አስተያየት ግኝቶቹ የአገልግሎት መ/ቤቱን ቀጣይ ስራዎች ለማጠናከርና ይበልጥ ለማሻሻል የሚረዱ መሆናቸውን በዝርዝር አስቀምጠው ሚኒስቴር መ/ቤታቸው በተቋሙ አሠራር ላይ እያደረገ ያለውን የክትትልና ድጋፍ ተግባር የኦዲት ግኝቶቹን መሠረት ባደረገ መልኩ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሠ አገልግሎት መ/ቤቱ አዘጋጅቶ የላከውን የኦዲት ግኝት ማስተካከያ የድርጊት መርሀ ግብር መሠረት አድርገው ባቀረቡት አስተያየት በግኝቶቹ ላይ ተወሰዱ የተባሉት የማስተካከያ እርምጃዎች በቀጣይ የክትትል ኦዲት የሚረጋገጡ መሆኑን ጠቅሰው ግኝቶቹ ተቋሙ በተለይ በመረጃና ማስረጃ አያያዝ ረገድ ያለበትን ጉልህ ክፍተት ያሳዩ በመሆናቸው የተጠናከረ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡
በእቅድ ዝግጅትና ግዥ ሥርዓቱ ላይ እንዲሁም ልዩ የአቅርቦት ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው የእናቶች፣ ህጻናትና አካል ጉዳተኞች የመድሃኒትና የህክምና መሳሪያ ስርጭት ረገድ ያሉ ክፍተቶች የበለጠ ትኩረት እንዲሰጣቸው ጨምረው ያሳሰቡት ክቡር አቶ አበራ ታደሠ በቁጥጥርና ክትትል ስርኣት እንዲሁም በመድሃኒት ማከማቻ መጋዘኖች ምቹነትና ተገቢነት ላይም ቀጣይ እርምጃዎች መወሰድ እንደሚኖርባቸው ገልጸው በመድሃኒትና በህክምና ግብአቶች ብክነት መንስኤ እና በተገልጋዮች እርካታ ረገድ ጥናቶች እንደሚያስፈልጉ እና በተለይ በዱቤ ገቢ አሳባሰብ ረገድ በወቅቱ የዱቤ ሂሳባቸውን ገቢ ባለደረጉ አካላት ላይ ህግና መመሪያን የተከተለ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው በኦዲቱ ጅማሮ ላይ ከተቋሙ ጋር ስምምነት የተደረገባቸው የኦዲት ሂደት መስፈርቶች እንደነበሩ በማስታወስ እና ተቋሙ ቀደም ሲል በ2008 ዓ.ም ለተካሄደው ተመሳሳይ የክዋኔ ኦዲት ግኝቶቹን በማስተካከል ረገድ የሰጠውን አጥጋቢ ያልሆነ ምላሽና በአሁኑ ኦዲት ለታዩት ግኝቶች የተሰጡ አዎንታዊ ምላሾችንና እየተደረጉ ያሉ የተሻሻሉ አበረታች ጥረቶችን በማነጻጸር አስተያየት የሰጡ ሲሆን ለእቅድ ዝግጅትና ትግበራ እንዲሁም ለአቅርቦትና ለፍላጎት መጣጣም መሠረት በሆነው የቅድመ ትንበያ ስራ ላይ ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው ትንበያዎች በጥናት የተደገፉ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል፡፡
እናቶች፣ ህጻናትና አካል ጉዳተኞች ልዩ እገዛ የሚያስፈልጋቸው በመሆናቸው የሚደረጉላቸው የመድሃኒትም ሆነ ሌሎች የህክምና ግብአት አቅርቦቶች በተለየ ሁኔታ ሊታዩ እንደሚገባ ጨምረው የገለጹት ክብርት ዋና ኦዲተሯ የተቋሙ የአገልግሎት አሠጣጥ ባህሪ የተለየ ቢሆንም የግዥ ስርዓቱ ከሀገሪቱ የግዥ መመሪያ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን አሳስበዋል፡፡
የእርምት እርምጃ ተወስዶባቸዋል የተባሉ ግኝቶች ሁኔታ በክትትል ኦዲት የሚረጋገጥ መሆኑን በአስተያየታቸው ያነሱት ክብርት ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በመረጃ አያያዝ፣ በግዥ ስርዓት፣ በአመታዊ የንብረት ቆጠራ እና ተከታታይ የውስጥ ኦዲት ስራዎችን በመስራት ረገድ ቀጣይ የተጠናከሩ ጥረቶች እንደሚያስፈልጉ ጠቅሰው መድሃኒቶችና የህክምና መገልገያዎች ከቦታ ወደ ቦታ በሚዘዋወሩበት ወቅት ከባህሪያቸው አንጻር የተለየ እንክብካቤ፣ ጥበቃና ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግና በመድሃኒት እና የህክምና ቁሳቁስ አቅርቦትና ስርጭት ሂደት እስከታችኞቹ የጤና ማዕከላት ድረስ ዘመናዊ የሆነ ዲጂታላይዝድ አሠራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት የኦዲት ግኝቶቹን መሠረት ያደረጉ የእርምት እርምጃዎችን መውሰዱ በበጎ የሚታይና አበረታች መሆኑን በማስቀደም የማጠቃለያ አስተያየት የሰጡት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ የሺመቤት ደምሴ(ዶ.ር) በበኩላቸው በውይይት መድረኩ በዝርዝር የቀረቡ የኦዲት ግኝቶችንና ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትም ሆነ ከመድረኩ የተሰጡ የማሻሻያ አስተያየቶችን በመወሰድ በቀሪ ግኝቶች ላይ ቀጣይ ስራዎች እንዲተገበሩ አሳስበዋል፡፡ አክለውም በቀጣይ እርምጃ የተወሰደባቸውን ግኝቶች ማረጋገጫ የድጋፍና ክትትል የመስክ ምልከታ በቋሚ ኮሚቴው እንደሚካሄድ ጠቅሰው ቀሪ ግኝቶችን ለማስተካከል የሚወሰዱ ተጨማሪ እርምጃዎች አፈጻጸምን የሚመለከት ሪፖረት በየሶስት ወሩ እንዲቀርብ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡