News

አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከተደጋጋሚ የኦዲት ግኝት ራሱን ነጻ ማድረግ እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከተደጋጋሚ አሉታዊ የኦዲት ግኝት ነጻ እንዲሆን አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በዩኒቨርስቲው ዋናው ግቢ፣ በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እንዲሁም በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ላይ የዋና ኦዲተር መ/ቤት ባደረገው የ2008 በጀት አመት የሂሳብ ኦዲት ላይ ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ ግንቦት 16/2010 ዓ.ም አካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ ሶስቱም ተቋማት በፋይናንስ አስተዳደር፣ በግዥ አፈጻጸምና በንብረት አያያዝ በኩል ያሉባቸው ችግሮች በዝርዝር ቀርበዋል፡፡

በተሰብሳቢ ሂሳብ ረገድ በበጀት አመቱ በዋናው ግቢ ብር 679,376,980.06፤ በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ  ብር 39,412,282.8 ፣ በቴክኖሎጂ እንስቲትዩት ደግሞ ብር 15,750,380.81 በወቅቱ ያልተወራረደና ያልተሰበሰበ ሂሳብ እንዳለ ኦዲቱ አሳይቷል፡፡ እንደዚሁም በዋናው ግቢ ብር 1,989,350.20፣ በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ  ብር 6,474,452.04፣ በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ደግሞ ብር 14,538,178,25 ለተለያዩ ክፍያዎች በሚል ከመመሪያ ውጪ ተከፍሏል፡፡ እንደዚሁም ሶስቱም ተቋማት ሌሎች የፋይናንስ ስርአቱን ያልጠበቁ ተግባራትን እንዳከናወኑ፣ መመሪያን ያልተከተሉ ግዥዎችን ከተለያዩ አካላት እንደፈጸሙና በንብረት አያያዝ በኩል ድክመት እንዳሳዩ ኦዲቱ በዝርዝር አመልክቷል፡፡

የዩኒቨርስቲው የአስተዳደር ምክትል ፕሬዘዳንት ዶ/ር ማቲያስ ኢንሰርሙና የየተቋማቱ ሌሎች ኃላፊዎች በኦዲት ግኝቶቹ ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ዩኒቨርስቲው ከኦዲቱ በኋላ ችግሮቹን ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ አኳያ በዋናነት የተሰብሳቢ ሂሳቦችን ወደኋላ ሄዶ የማጣራት፣ አላግባብ የሚከፈሉ ክፍያዎችን የማቋረጥ፣ ተመን ላልነበራቸው ስራዎች ተመን የማውጣት፣ ወደተሻለ የፋይናንስ ስርአት ለመግባት ጥረት የማድረግና ንብረቶችን የማስወገድና ሌሎች ተያያዥ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው አሰራሮችን ለማስተካከል የተጀመሩ ስራዎችን በበጎ ጎን ወስዶ ነገር ግን  ዩኒቨርስቲው እንደአንጋፋ የምሁራን መፍለቂያና የምርምር ተቋምነቱ ያሉበትን ችግሮች ፈትሾ መፍትሄ የመስጠት አቅም እንዳለው በመጥቀስ በተደጋጋሚ የሚታዩበትንና እየጨመሩ ያሉ የኦዲት ችግሮች ፈትቶ  ከአሉታዊ የኦዲት ግኝቶች የጸዳ አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ተቋም እንዲሆን አመራሩ ራሱን በመፈተሽ በበለጠ ቁርጠኝነትና የባለቤትነት ስሜት መስራት እንዳለበት አሳስቧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *