Uncategorized

ተገቢ የፕሮጀክት አዋጭነትና የአካባቢ ተጽዕኖ ጥናት ያለመደረጉ ተጨማሪ ወጪ ማስከተሉ ተገለጸ

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ እያስገነባቸው ባሉ የእናቶችና ህጻናት እንዲሁም የልብ፣ የአንጀትና የካንሰር ህክምና ማዕከል የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ተገቢ የሆነ የአዋጭነትና የአካባቢ ጥበቃ ተጽዕኖ ጥናት ባለመደረጉ ለፕሮጀክቶቹ ከተመደበው በጀት በላይ ወጪ ማስከተሉና ግንባታዎቹ ከታቀደላቸው የማጠናቀቂያ ጊዜ በላይ መፍጀታቸው ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም ላይ በ2013/2014 በጀት ዓመት ባካሄደው የክዋኔ ኦዲት በታዩ የኦዲት ግኝቶች ላይ ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ነው፡፡

ተገቢ የሆነ ቅድመ የአዋጭነትና የአካባቢ ጥበቃ ተጽዕኖ ጥናት ባለመደረጉ በፕሮጀክቶቹ ላይ የተጋነነና ተደጋጋሚ የሆነ የዲዛይን ማሻሻያዎች እንዲደረጉ እና በዚህም ሳቢያ ለፕሮጀክቶቹ ከተመደበው በጀት በላይ ወጪን ከማስከተል አልፎ የማጠናቀቂያ ጊዜ መራዘም ማስከተሉ በመድረኩ ላይ ተነስቷል፡፡

የቴክኒካል ግምገማ ሳይደረግ በፋይናንስ አቅም ግምገማ ብቻ ተቋራጮችን ለግንባታ ጨረታ ውድድር ማስገባትን ጨምሮ ሌሎች በፕሮጀክት መመሪያና ማኑዋል አዘገጃጀትና አተገባበር፣ በሰው ኃይል እና መዋቅር፣ በሪፖርት አቀራረብና በሌሎች አፈጻጸሞች ላይ ጉልህ ክፍተቶች መታየታቸውን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ሪፖርት ማሳየቱ ተነስቷል፡፡

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ፕሮቮሰት ሲሳይ ስርጉ (ዶ.ር) እና የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አየለ ተሾመ (ዶ.ር) በተነሱት የኦዲት ግኝቶች ላይ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የኢዲት ግኝቶቹ ትክክለኛ መሆናቸውንና በበርካታ ግኝቶች ላይ የማሻሻያ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ጠቁመው ቀጣይ ስራዎች በተሰጡ አስተያየቶች መሰረት ታርመው እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡

በፕሮጀክቶቹ ላይ የተደረጉት ተደጋጋሚ የዲዛይን ማሻሻያዎች የመጀመሪዎቹ ዲዛይኖች ከረጅም ጊዜ በፊት የተሰሩ በመሆናቸውና በጊዜ ሂደት የሚጎሏቸው ነገሮች እንዳሉ በመታወቁ የተከሰቱ መሆናቸውን ጨምረው የገለጹት የስራ ኃላፊዎቹ ተደጋጋሚ የዲዛይን ስራና የማሻሻያ ስራዎች የተከሰቱት የህንጻዎቹ ወለል ብዛት እንዲጨምር በመደረጉ፣ በግንባታ ቦታ መሻሻል፣ ቀደም ሲል በቂ ዕውቀት ባለመኖሩ እና ከአለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ በተሰጠው ቴክኒካል አስተያየት መሰረት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ተደጋጋሚ የዲዛይን ማሻሻያ ስራ እንዲከሰትና ለተጨማሪ በጀትና የጊዜ ብክነት ምክንያት የሆነው ተገቢ የሆነ የአዋጭነት ጥናት ያለመደረጉ መሆኑን በአስተያየታቸው የገለጹት የቋሚ ኮሚቴው አባላትና ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው የግንባታ ተቋራጮችን ህጋዊ ባለሆነ አሠራር የጨረታ ውድድር አካል አድርጎ ማስገባት ህገ ወጥነት ነው ብለዋል፡፡

አክለውም በአሠራር ክፍተት ፕሮጀክቶቹን ለተጨማሪ ወጪና ጊዜ የዳረጉ አካላትም መጠየቅ አለባቸው ብለዋል፡፡

የማሻሻያ እርምጃ የተወሰደባቸው ግኝቶች በቀጣይ በሚደረግ የክትትል ኦዲት የሚረጋገጡ መሆኑን በማንሳት አስተያየታቸውን የሰጡት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ በበኩላቸው በፕሮጀክቶች ላይ የአዋጭነትና የአካባቢ ጥበቃ ጥናት ያለመደረጉ ተደጋጋሚ የዲዛይን ክለሳ እንዲደረግ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው በግንባታ ተቋራጮች ላይ የሚደረግ የቅድመ ብቃት እና ድህረ ብቃት ግምገማ ለግንባታ ፕሮጀክቶች ጥራት አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ የፌዴራል ዋና ኦዲተር በበኩላቸው በጨረታ ሂደት ቅድሚያ መሰጠት ያለበት የቴክኒካል ግምገማ መሆኑንና በውስን ጨረታ ሂደት በፋይናንስ አቅም ግምገማ ብቻ ተቋራጮችን ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ ህገ ወጥ አሠራር መሆኑን ገለጸው ጨረታው በውስን ጨረታ መካሄዱ የፕሮጀክቶቹን አፈጻጸም ከገንዘብና ከጊዜ ተጨማሪ ወጪ አልታደገም ብለዋል፡፡

አክለውም የቅድመ አዋጭነትና የአካባቢ ጥበቃ ጥናቶች ያላቸውን ጠቀሜታ ተቋሙ እያከናወናቸው ባሉ ሌሎች የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይም ማረጋገጥ እንዳለበት እንዲሁም የዲዛይን ማሻሻያ ማድረግ የተለመደ አሠራር ቢሆንም ህግን ያልተከተለና በተጋነነ ሁኔታ ተደጋግሞ መደረጉ ተጨማሪ የበጀት ወጪ የጠየቀና የጊዜ ብክነትም ያስከተለ በመሆኑ ሆን ተብሎ መመሪያን በጣሱ አካላት ላይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ክብርት ዋና ኦዲተሯ ገልጸዋል፡፡

የማጠቃለያ አስተያየታቸውን የሰጡት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስትያን ታደለ በፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም ላይ የመንግስትን አሠራር፣ ህግና መመሪያን የጣሱ እንዲሁም ለሙስናና ብልሹ አሠራር ሊያጋልጡ የሚችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው የአዋጭነትና የአካባቢ ተጽዕኖ ጥናት ያለመደረጉ እና በጨረታ ሂደት የታዩ የአሠራር ችግሮች የተቋሙ ክፍተቶች ናቸው ብለዋል፡፡

ተቋሙ በመድረኩ የተነሱ የማሻሻያ አስተያየቶችን መሰረት ያደረገ አዲስ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ የድርጊት መርሀ ግብር በ10 ቀናት ውስጥ አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ አቅጣጫ የሰጡት ሰብሳቢው የአሠራር መመሪያዎች ተግባራዊ ኢንዲሆኑና በግንባታ ፕሮጀክቶቹ ላይ ችግር የፈጠሩ አካላት ላይ የተጠያቂነት እርምጃዎች እንዲወሰዱም ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *