News

ተቋሙ በግዥ አፈጻጸም፣ በወጪሥርዓት እና በንብረት አያያዝና አስተዳደር አሠራሩ ላይ ያሉበትን ክፍተቶች እንዲያርም ተጠየቀ

የቀድሞው የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብአቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲቲዩት በአሁኑ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲቲዩት የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብአቶች ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል በግዥ አፈጻጸም፣ በአበልና መስተንግዶ ወጪ እንዲሁም በንብረት አያያዝና አስተዳደር አሠራሩ ላይ ያሉበትን ክፍተቶች ማስተካከል እንዳለበት ተጠየቀ፡፡

ይህ የተጠየቀው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተቋሙ ላይ ያደረገውን የ2013 በጀት ዓመት የሂሳብ ህጋዊነት ኦዲት መነሻ በማድረግ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  ታህሳስ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ነው፡፡

የኦዲት ሪፖርቱን መነሻ በማድረግ የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ባነሷቸው ጥያቄዎችና ባቀረቡት ሀሳብ መሰረት በርካታ ህጋዊነትን ያልተከተሉ የግዥ፣ የጨረታ እና የአበል አከፋፈል አሠራሮች በተቋሙ ላይ የታዩ ሲሆን ከ ብር 1.2 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ግዥ ህጋዊ ባልሆነ የግዥ አካሄድ መፈጸሙ፣ በብር 308,532,.64 ህጋዊና አስፈላጊ ሰነዶች ያልቀረቡበት የአገልግሎት ግዥ መከናወኑ፣ በተፈላጊ ባህርያት ዝርዝር (Specifcation) ያልተረጋገጠ ከብር 1 ሚሊዮን በላይ ግዥ መፈጸሙ፣ ከብር 8.9 ሚሊዮን  በላይ ህጋዊ ሥርዓቱን ያልተከተለ ጨረታ አካ መከናወኑ እና ሌሎች ህጋዊነትን ያልተከተሉ ግዥዎች ተፈጽመዋል፡፡

ከዚህም ሌላ የመንግስትን የወጪ ቅነሳ ሥርዓት የሚጥሱና ህጋዊ ያልሆኑ የመስተንግዶ ወጪዎች ተከፍለው መገኘታቸው እና በክትትል ኦዲቱ መሠረትም አግባብ ያልሆኑ የአበል ክፍያዎች ተከፍለው መገኘታቸው በመድረኩ ላይ ተነስቷል፡፡

በተጨማሪም ጥቂት የማይባሉ የንብረት አያያዝና አስተዳደር ሥርዓት ክፍተቶች መታየታቸው ተጠቅሷል፡፡

በመድረኩ ላይ በመገኘት የኦዲት ግኝቶቹን በሚመለከት ምላሽ የሰጡት የማዕከሉ አመራሮች  አብዛኛዎቹ በሂሳብና በንብረት አያያዝና አስተዳደር ረገድ በታዩት የኦዲት ግኝቶች ላይ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ተቋሙ በመጀመሪያ ደረጃ በተደረገው ኦዲቲም ሆነ በክትትል ኦዲቱ ወቅት በርካታ የግዥ፣ የክፍያ፣ የጨረታ፣ የአበል እንዲሁም ሌሎች የንብረት አያያዝና አስተዳደር ክፍተቶች የታዩ መሆኑንና እስካሁንም ድረስ ያልተስተካከሉ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ ትክክለኛውን መስመር መያዝ እና በየደረጃው በሚገኙ አጥፊዎች ላይ ተጠያቂነትን ሊያሰፍን እንደሚገባ ጨምረው የገለጹት ዋና ኦዲተሯ ህገወጥ አሠራሮችን ሊያስተካክሉ የሚችሉ  አፋጣኝ እርምጃዎችን መውሰድ  ከማዕከሉ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ አክለውም ማዕከሉ ተጠሪ የሆነለትና ጉዳዩ የሚመለከተው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም በማዕከሉ የተፈጸሙ ህገ ወጥ አሠራሮችን ለማስተካከል የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙ የቋሚ ኮሚቴ አባላት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በማዕከሉ የተፈጸሙ ህገ ወጥ አሠራረሮች ከተቋሙ አልፈው ሀገርን የሚጎዱ በመሆናቸው በአፋጣኝ መታረም አለባቸው ብለዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው የኦዲት ግኝቶቹ ትክክለኛና መታረም ያለባቸው በመሆኑ የሚኒስቴር መ/ቤታቸው የማዕከሉን ህገወጥ አሠራር ለማስተካከል አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ ይወስዳል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስትያን ታደለ ተቋሙ በበጀት አጠቃቀም፣ በንብረት አያያዝና አስተዳደር እንዲሁም በስነ ምግባር ረገድ በርካታ ግድፈቶች ያሉበት በመሆኑ ማዕከሉና ተጠሪ የሆነለት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ችግሮቹን በአስቸኳይ ማስተካከል አለባቸው ብለዋል፡፡

አክለውም ማዕከሉ እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2015 ድረስ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ መርሀ ግብር እና ሪፖርት እንዲያቀርብና በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላትም በሚመለከታቸው ጉዳዮች ዙሪያ የማስተካከያ እርምጃ በሚወሰድበት ሁኔታ ላይ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *