News

ቦርዱ የኦዲት ግኝቶቹን ለማስተካከል እያደረገ ያለውን ጥረት እንዲያጠናክር ተጠየቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የ2015/2016 ኦዲት አመት የፋይናንሽያል ኦዲት መሠረት የታዩበትን የሂሳብና ንብረት አስተዳደር አሠራር ክፍተቶች ለማስተካከል እያደረገ ያለውን ጥረት ይበልጥ ማጠናከር እንደሚኖርበት ተገለጸ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ህዳር 11 ቀን 2017 ዓ.ም ባካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት መድረክ ቀደም ሲል ከ2009 አስከ 2014 በጀት አመት በተደረጉ ኦዲቶች በቦርዱ ላይ ከታዩ ግኝቶች አስከ አሁን እርምጃ ያልተወሰደባቸው መኖራቸው ተጠቅሷል፡፡

በ2015 በጀት አመት የቦርዱ የሂሳብ ኦዲት ውጤት መሰረትም ከብር 1.2 ሚሊዮን በላይ ለተሸከርካሪ ነዳጅ ተከፈለ ለተባለ ክፍያ ህጋዊ ደረሰኝ ያለመቅረቡ፣ ከብር 8.5 ሚሊዮን በላይ ከማን እንደሚሰበሰብ የሚገልጽ መነሻ የምዝገባ ሰነድ ያልቀረበበት ተሰብሳቢ እንዲሁም ከብር 981.3 ሺህ በላይ መነሻ የምዝገባ ሰነድ ያልቀረበበት ተከፋይ ሂሳቦች መገኘታቸውን ጨምሮ ሌሎች በወቅቱ ያልተወራረዱ ከብር 17.8 ሚሊዮን በላይ ተሰብሳቢና ከብር 7.5 ሚሊዮን በላይ ተከፋይ ውዝፍ ሂሳቦች መገኘታቸው በመድረኩ ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይ ከብር 6.5 ሚሊዮን በላይ በተገቢ የሂሳብ መደብ ያልተመዘገበ የወጪ ሂሳብ መታየቱ ፣ ለበጀት አመቱ ከተፈቀደው መደበኛ በጀት ከብር 19.9 ሚሊዮን በላይ በስራ ላይ ሳይውል መገኘቱ እና የግዥና ክፍያ አፈጻጸም እንዲሁም የንብረት አስተዳደር እና ሌሎች አሠራሮችን የተመለከቱ ግኝቶች በዝርዝር ቀርበው የቋሚ ኮሚቴ አባላቱና የኦዲት ባለድርሻ አካላት እርምጃ ያልተወሰደባቸው የኦዲት ግኝቶች እንዲስተካከሉና መሻሻሎች እንዲጠናከሩ አስተያየቶቻቸውን ሰጥተዋል፡፡

ከመድረኩ የተነሱትን አስተያየቶች አስመልክቶ የቦርዱ አመራሮች ለግኝቶቹ ምላሽ ያሏቸውን ሀሳቦችና የተወሰዱ የማስተካከያ እርምጃዎችን ያቀረቡ ሲሆን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሠ በሰጡት አስተያየት በንብረት አስተዳደር ላይ የታዩ ግኝቶችን ለማስተካከል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን በበጎ መልኩ አንስተው በእቅድ የሚመራ የበጀት አጠቃቀም ሊኖር እንደሚገባና ከኦዲቱ በኋላ በተደረገ የኦዲት ክትትል ስራ አሁንም አብዛኞቹ የኦዲት ግንቶች ያልተስተካከሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተለይ የሂሳብ ሰነድ ማስረጃዎች በቂ እና ተገቢ መሆናቸውን ማረጋገጥ የኦዲቱ ተግባር መሆኑን የጠቀሱት ክቡር አቶ አበራ ቦርዱ ተገቢና የተሟሉ የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ ግኝቶቹን ማስተካከልና ህጋዊ መመሪያን የተከተለ የፋይናንስ ስርዓቱን ማጠናከር አለበት ብለዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው የኦዲቱ ትኩረት በበጀት አመቱ የታዩና ያልተስተካከሉ አሠራሮች ላይ ቢሆንም ከኋላ ተንከባለው የመጡና እርምጃ ያልተወሰደባቸው ግኝቶች ካሉም እነሱን ማረጋገጥና አስተያየት መስጠት የኦዲቱ አካል ነው ብለዋል፡፡

በንብረት አስተዳደር ላይ የነበሩ ክፍተቶችን ለማስወገድ ቦርዱ ጥረት እያደረገ መሆኑ አበረታች መሆኑን በማንሳት ለኦዲት ግኝቶቹ ከተሰጡ አስተያየቶች በኋላ በተደረጉ የክትትል ኦዲቶች አሁንም ድረስ ያልተስተካከሉ አሠራሮች መኖራቸውን የጠቀሱት ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ቦርዱ በተከፋይና ተሰብሳቢ ሂሳቦች፣ በበጀት አጠቃቀም፣ በሠራተኞች አስተዳደር ደንብ ትግበራ የሚታዩ ችግሮችን መፍታትና ተገቢ የመንግስት አሠራርን መከተልና ህግና መመሪያን መተግበርም ከቦርዱ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ቀጣይ የኦዲት ግኝት ማስተካከያ እርምጃዎች ተወስደው በአጭር ጊዜ ውስጥ ለተገቢ አካላት የአፈጻጸም ሪፖርት እንዲቀርብ ለቦርዱ አመራሮች አቅጣጫ በማስቀመጥ የማጠቃለያ አስተያየት የሰጡት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ የሺመቤት ደምሴ (ዶ.ር) ለትክክለኛና ህጋዊ አሠራር ኦዲት ያለውን ጠቀሜታ በማንሳት ቦርዱ ለግኝቶቹ ትኩረት መስጠት እና በተለይም መንግስት ያወጣቸውን የሂሳብ አሠራሮችን፣ ህጎችንና መመሪያዎችን መከተልና ማስረጃ ባልቀረበባቸው ተከፋይና ተሰብሳቢ ሂሳቦች ላይ ማስተካከያ በመውሰድ ሂሳቦቹን በተገቢና በተሟላ ሰነድ ህጋዊ ማድረግ ቀጣይ የቦርዱ ተግባር መሆን እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡

 

The Public Hearing Demands More Improvement Actions on the Board Audit Findings

The public hearing, organized by the Standing Committee of the Public Expenditure Administration and Controlling Affairs in the Ethiopian Parliament, held on Nov 20/2024, claimed more corrective measures to be taken on the audit findings of the Ethiopian National Electoral Board.

Based on the 2023/2024 financial audit report of the Office of the Federal Auditor General, the joint gathering of the standing committee and other audit stakeholders discussed several audit findings shown in the financial and property administration systems of the Board.

Selected findings from the entire audit report revealed that the Board violated several financial and property administration directives, regulations & working systems in its 2015 Ethiopian fiscal year.

In addition to commented but unimproved findings of the previous audits in the financial and property administration systems of the board, inappropriate payments, misuse of allocated budgets, illegal procurements, improper utilization and management of properties and other critical gaps have been found in the last fiscal year, the findings discussed in the public hearing indicated.

After applicable corrective suggestions given by the standing committee members and the stakeholders on the findings, H.E. Mrs. Meseret Damtie, the Federal Auditor General and H.E. Mr. Abera Tadesse, Deputy Auditor General, OFAG proposed valid and workable comments and propositions to the Board officials in order to take extra measures that can basically minimize the short comings mainly seen in the financial systems of the Board.

Ended, the OFAG officials recommended that organizing and handling the appropriate and valid working documents; implementing legal human resource, financial and property administration regulations and orders; timely and proper utilization of allocated budgets and other related working strategies and techniques should have been employed in order to improve the findings.

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *