News

ባለስልጣን መ/ቤቱ ህጎችንና የአሠራር ሥርዓቶችን ተፈጻሚ እንዲሆኑ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ተገለጸ

የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን ደንብና መመሪያዎችን ተፈጻሚ ከማድረግ እንዲሁም ሌሎች የአሠራር ሥርዓቶች ተከትሎ ሥራዎችን ከመስራት አንጻር የታዩ ክፍተቶችን ሊቀርፍ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መጋቢት 27 ቀን 2015 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን /የቀድሞ የጨረራ መከላከል ባለስልጣን/ የጨረር አመንጪ ቁሶች ፈቀድ አሰጣጥና ቁጥጥር አፈጻጸምን በተመለከተ የ2013/2014 የተከናወነ የክዋኔ ኦዲት መነሻ በማድረግ ይፋዊ ህዝባዊ የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡

በመድረኩ የጨረራና ኒውክለር መከላከያ አዋጅ ቁጥር 1025/2009 ተከትሎ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ረቂቅ ደንብ ቢያዘጋጅም ደንቡን አጸድቆ ወደሥራ አለመግባቱን፣ ተቋማት የጨረራ አመንጪ ቁሶች የመጠቀሚያ ፈቃድ እንዲሁም የታደሰ የፈቃድ ምስክር ወረቀት ሳይኖራቸው የጨረራ አመንጪ ቁሶችን ጥቅም ላይ እንደሚያውሉ እና የጨረራ አመንጪ መሣሪያዎች የሚለቁት የጨረራ መጠን ትክክለኛ መሆኑን በሚመለከተው ተቋም መደበኛ ፍተሻ በማድረግ እንደማያረጋግጥ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል ተቋማት የሚጠቀሙባቸውን የጨረራ አመንጪ መሣሪያዎች ጥገና ሲያስደርጉ እና ሲያስወግዱ እንደማያሳውቁ፣ በተቋሙ ጥናትና ምርምር አለመስራቱን፣ የጨረራ አመንጪ ቁሶችን እና ተዛማች ተግባራትን በተዘረጋ ሥርዓት አለመመዝገቡን፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ቢፈራረምም በስምምነቱ መሠረት አለመስራቱን እና ሌሎች ማከናወን ይገባቸው የነበሩ ተግባራትን በአግባቡ አለማከናወኑ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሠለሞን ጌታቸው በበኩላቸው አዋጅ ቁጥር 1025/2009 ተከትሎ ወደሥራ መግባት የነበረበት ደንብ በእነሱ በኩል ተዘጋጅቶና በሚመለከተው አካል በየደረጃው ታይቶ የተጠናቀቀ ቢሆንም በሚኒስትሮች ምክርቤት ባለመጽደቁ ተፈጻሚ ለማድረግ መቸገራቸውን አስረድተዋል፡፡

ተቋማት ፈቃድ ኖራቸው የጨረራ አመንጪ ቁሶችን ጥቅም ላይ እንዲያውሉ ከማድረግ አኳያ በኦዲቱ ወቅት በጸጥታና እና በኮቪድ ወረረሽኝ ምክንያት ክትትል ለማድረግ አለመቻላቸውን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡

የሚለቁት የጨረራ መጠን ትክክለኛነት ከማረጋገጥ አንጻርም ሥራው የሚከናወነው በኢትዮጵያ የስነ-ልክ ኢንስቲትዩት በመሆኑ እና በኢንስቲዩቱ ያለው የመፈተሻ መሣሪያ ለረጅም ጊዜ ተበላሽቶ በመቀመጡ ተገቢውን መደበኛ ፍተሻ ለማድረግ መቸገራቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከጥናትና ምርምር ጋር በተያያዘም ባለሥልጣን መ/ቤቱ በዘርፉ በርካታ የምርምር ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅበት አንስተው ከዚህ አንጻር ጥሩ እየሠሩ እንደሆነና በተለይም ከዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጋር እንደሚሠሩ አንስተዋል፡፡

ከባለድርሻ አካላት ጋር በተያያዘ በኦዲቱ የታየው ክፍተት ተክክለኛ መሆኑን እና ሌሎች በኦዲት ሪፖርቱ የተመላከቱ ግኝቶችን በቀጣይ የእቅዳቸው አካል አድርገው እንደሚሠሩ አስረድተዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ምክትል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ በበኩላቸው ባለስልጣን መ/ቤቱ የጨረራ ዝቃጭ ቁሶች አወጋገድ እና ደህንነት ደንብ አጸድቆ ወደሥራ ለማስገባት የወሰደበት ጊዜ በጣም የተራዘመ መሆኑን ጠቁመው ደንቡ ጸድቆ በፍጥነት ወደ ስራ መግባት አለበት ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር የጨረራና ኒውክለር ቁጥጥር ባለሥልጣን ማቋቋሚያ አዋጅን እና ሌሎች ህጎችን በሚገባ ለማስፈጸም ከተዘጋጁ 13 መመሪያዎች መካከል ወደ ሥራ የገቡት 3 ብቻ መሆናቸው በኦዲት መረጋገጡን ጠቅሰዋል።

እነዚህ መመሪያዎች ባለሥልጣኑ ወጤታማ ሥራ እንዲያከናውን የሚያግዙ በመሆናቸው ያልጸደቁ መመሪያዎች በፍጥነት ማጸደቅ ላይ በትኩረት ሊሰሩበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው ያለፈቃድ ጨረራ አመንጪ ቁሶችን ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡ አካላት ላይ ክፍተኛ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወይዘሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው የጨረራና ኒውክሌር መከላከያ አዋጅ ቁጥር 1025/2009 መሰረት በማድረግ የጨረራ አመንጪ መሳሪያዎችን በሚመለከት የማሳወቅና ፈቃድ የማግኘት ግዴታዎች፣ እንዲሁም ቁጥጥርና ክትትልን የሚመራ ደንብ አለመውጣቱን እና ደንቡን ሳያጸድቅ ለ7 ተቋማት ፈቃድ መስጠቱና ሌሎች 15 ተቋማት ደግሞ ፈቃድ ሳይኖራቸው እየሰሩ እንደሚገኙም አንስተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ባለሥልጣን መ/ቤቱ የካሊብሬሽን ሥራ እና የኢንስፔክሽን ሥራ በተሟላ ሁኔታ እያከናወነ አለመሆኑን እና በጨረራ ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች የጤና ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸው በመመሪያው ላይ ቢቀመጥም የአፈጻጸም ውስንነት መኖሩን ዋና ኦዲተሯ ገለፀዋል።

አክለውም የመንግስትም ይሁን የግል ሆስፒታሎች ጨረራ አመንጪ መሳሪያዎችን ሲያስጠግኑም ሆነ ሲያስወግዱ ባለስልጣኑ እንዲያውቀው ማድረግ ላይ ሰፊ ክፍተት በመኖሩ በህብረተሰብ ጤና ላይ ትልቅ ችግር ሊያመጣ የሚችል በመሆኑ ትኩረት እንደሚያስፈልገውም ጠቁመዋል።

በመጨረሻ አስተያየታቸውን የሰጡት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መሥራትና ከሕዝብ የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣትእንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የድርጊት መርሃግብር በ10 ቀናት ውስጥ አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ፣ በ2 ወራት ጊዜ ውስጥ ደንቡን አፀድቆ ተግባራዊ እንዲያደርግ፣ የኢንስፔክሽን ሥራዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ከባለድርሻ ጋር ያለሁን የመግባቢያ ስምምነት በአስገዳጅ መልኩ ዳግም ከልሶ በ2 ወራት ጊዜ ውስጥ እንዲሁም የኦዲት ማሻሺያዎችን በየ 3 ወሩ ሪፖርት እንዲያቀርብ አሳስበው ለሌሎችም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነት ተወጥተው ሪፖርት እንዲያደርጉ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *