የጋራ የኦዲት ሥራን የበለጠ የሚያጠናክር የፌዴራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች 22ኛ ጉባኤ ሐምሌ 8 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዋና ከተማ ቦንጋ ተካሂዷል፡፡
በጉባኤው የፌዴራል፣ የክልሎችና የሁለቱ የፌዴራል ከተሞች አስተዳደር ዋና ኦዲተሮች እና ምክትል ዋና ኦዲተሮች እንዲሁም ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዋና አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ 22ኛው የዋና ኦዲተሮች ጉባኤ በክልላቸው ዋና ከተማ ቦንጋ በመካሄዱ ደስተኛ መሆናቸውን ጠቁመው የክልሉ ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆንም መ/ቤቱ በክልሉ ከሚገኙ ጠንካራ ተቋማት ግንባር ቀደሙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም የክልሉ ዋና ኦዲተር መ/ቤት ባለሙያዎች አዳዲስ ከመሆናቸው አንጻር ክልሉ በራሱና ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን የተጠናከረ የአቅም ግንባታ ስልጠና እንዲያገኙ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አፈጉባኤው ገልጸዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር የተከበሩ ዶ/ር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው ክልሉም ሆነ የክልሉ ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከተመሰረቱ አጭር ጊዜ ቢሆንም ጠንካራ ሥራዎች እየሠሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በተለይም የክልሉ ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከሌሎች የስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና እንዲሁም ከህግ ተቋማት ጋር የተቀናጀ ትብብር በመፍጠር በርካታ ውጤታማ ሥራዎች መስራቱን የገለጹት ርዕሰ መስተዳደሩ እነዚህን ተቋማት በማጠናከር የመንግስትና የህዝብ ሀብት ያለአግባብ እንዳይባክንና በክልሉ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እየተከናወነ ያለው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የክልሉን ዋና ኦዲተር መ/ቤት አቅም በቴክኖሎጂ እና በአሠራር ሥርዓት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ለማጠናከር ክልሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል የተከበሩ ዶ/ር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ ገልጸው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለክልሉ ዋና ኦዲተር መ/ቤት እያደረገ ስላለው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ_መሠረት_ዳምጤ በበኩላቸው በመንግስት ተቋማት የሚፈጸሙ የሙስና እና ብልሹ አሠራሮች በከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱና የተገልጋዩን ህብረተሰብ ምሬት እያባባሱ ከመሆናቸው አንጻር በየደረጃው የሚገኙ ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ከህዝብና ከመንግስት የተሰጣቸውን ኃላፊነትና አደራ በብቃት ለመወጣት ትኩረት ሰጥተው መስራት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
በፌዴራልና በክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች የጋራ አሠራር ላይ እንቅፋት ሆኖ የቆየውን የኦዲት ድግግሞሽ ለማስቀረት የነጠላ ኦዲት አዋጅ እንዲወጣ መደረጉና በ3 ክልሎች እና በአንድ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች በሙከራ ደረጃ መተግበሩ በጠንካራ ጎኑ የሚታይ መሆኑንም ክብርት ዋና ኦዲተሯ አንስተዋል፡፡
22ኛው የዋና ኦዲተሮች ጉባኤ ባስቀመጠው የኦዲት ስራን ማጠናከሪያ የትግበራ አቅጣጫ መሰረት የሀገሪቱን የኦዲት አሠራር በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ወጥና ዓለም አቀፋዊ የኦዲት ስታንዳርዱን የጠበቀ ለማድረግ ቀጣይ ስራዎች መሰራት እንደሚገባቸውም ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ አሳስበዋል፡፡
ጉባኤው በሶስት ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ ያለውን የፌዴራል መንግስት ለክልሎች የሚሰጠውን የድጋፍና ድጎማ በጀት የተመለከተ የነጠላ ኦዲት አፈጻጸም የገመገመ ሲሆን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለክልልና ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች እያደረገ ያለውን ዘርፈ ብዙ ድጋፍ በተመለከተም ገለጻ ቀርቦ ጠቃሚ ውይይት ተደርጓል፡፡
በቀጣይ በጀት ዓመትም ሁሉም የፌዴራልና የክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች የነጠላ ኦዲትን ተግባራዊ ለማድረግ በጉባኤው ላይ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
በመጨረሻም በቀጣይ በሲዳማ ክልል ለሚካሄደው የዋና ኦዲተሮች ጉባኤ አጀንዳዎችን የሚቀርጽ ኮሚቴ በማወቀር ጉባኤው የተጠናቀቀ ሲሆን የጉባኤውን መጠናቀቅ ተከትሎ ሀምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ አረንጓዴ አሻራን የማኖር የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብር በጉባኤው ተሳታፊዎች ተካሂዷል፡፡
ተሳታፊዎቹ ከችግኝ ተከላ መርሀ ግብሩ በተጓዳኝ የቦንጋ ዩኒቨርሲቲን የስራ እንቅስቃሴ በመቃኘት በአካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ሀብትና ዩኒቨርሲቲው ለተለያዩ ምርምሮችና ለተማሪዎችና ለአካባቢው ህብረተሰብ በምግብ ፍጆታነት በጥቅም ላይ እያዋላቸው ያሉ የተለያዩ የግብርና የስራ እንቅስቃሴ ውጤቶችን ጎብኝተዋል፡፡