News

በውል ስምምነቱ መሰረት ፕሮጀክቶች ባለመጠናቀቃቸው የሀገር ሀብት እየባከነ መሆኑን ተጠቆመ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የፕሮጀክት ግንባታ አፈፃፀምን አስመልክቶ በ2013/14 በጀት ዓመት ባካሄደው የክዋኔ ኦዲት መሠረት በርካታ ሀብት እየባከነ መሆኑን ተገለጸ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም በኮርፖሬሽኑ ላይ የተሰራውን የኦዲት ሪፖርት መሠረት አድርጎ ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት አካሂዷል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከደንበኞች በውል የተረከባቸውን ፕሮጀክቶች ውል በተገባበት የጊዜ ገደብ ቶሎ ወደ ስራ  ያለማስገባት እና ያለማጠናቀቅ፣ የፕሮጀክቶች የግንባታ ደረጃ በየጊዜው ሪፖርት ሲደረግ መዋዥቅ ማሳየቱን፣ ከአንድ ዓመት እስከ አስራ ሰባት አመታት ያስቆጠሩ ተስብሳቢ ሂሳቦች መኖራቸው ተጠቁሟል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው የኦዲት ግኝቱ አስመልክተው በሰጡት ምላሽ ሁሉም ግኝቶቹ ከኮርፖሬሽኑ ሪፎርም በፊት የተፈጠሩ ችግሮች ቢሆኑም ኮርፖሬሽኑ ችግሮቹን ለመቅረፍ እየሰራ እንደሆነ ነገር ግን የተወሰኑት አሁንም የበላይ አካል ውሳኔ እንደሚያስፈልጋቸው አብራርተዋል፡፡

የቀረበው ማብራሪያና ምላሽ ጥቅል እንደሆነ፣ በኦዲት ግኝቱ መሠረት በዝርዝር እንዳልቀረበ እንዲሁም በእያንዳንዱ ግኝት ምን መፍትሄ እንደተወሰደ የማያመለክት መሆኑን የጠቆሙት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ አሁን ፕሮጀክቱ ያለበትን ደረጃ ኮርፖሬሽኑ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትና በመድረኩ የተገኙ ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው የቀረበው ማብራሪያና ምላሽ በቂ እንዳልሆነ ጠቅሰው ኮረፖሬሽኑ ውል ከመዋዋሉ በፊት ከፕሮጀክት የአዋጭነት ጥናት ጀምሮ እስከ ቁጥጥር እና ግምገማ ያለውን ሂደት በአግባቡ ባለመምራቱ በሀገር ሀብት ላይ ከፍተኛ ብክነትና ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው በሪፖርቱ የቀረቡ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ግዜ ገደብ ወደ ግንባታ ባለመግባታቸው ኮርፖሬሽኑን አላስፈላጊ ወጪ እያስወጡት እንደሚገኙ እና ህብረተሰቡም ማግኘት ያለበትን ጥቅም እንዳያገኝ ሁኗል ብለዋል፡፡

አያይዘውም መሰል ለፕሮጀክቶች ስምምነት ሲገባ ሀገርን እዳ ውስጥ የማይከቱ መሆናቸው ሊረጋገጥ እንደሚገባ እና የሚመለከታቸው አካላትም እንዲህ አይነት ስህተቶች በቀጣይ እንዳይደገሙ ከስር ከስር ቁጥጥርና ክትትል እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ አሁን ያለው የፕሮጀክት አፈፃፀም ጥሩ ቢሆንም ነገር ግን የበፊት ክፍተቶቹ ጥላ እያጠሉበት እንደሆነ ክብርት ዋና ኦዲተሯ ገልጸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኮርፖሬሽኑን ቢያግዙት አለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ ተቋም መፍጠር እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

በውይይቱ መጨረሻ አስተያየታቸውን የሰጡት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስትያን ታደለ በበኩላቸው የኦዲት ግኝቶቹ ኮረፖሬሽኑ በፕሮጀክት አስተዳደር ላይ ክፍተቶች እንዳሉበት ማሳያ በመሆናቸው የውል አስተዳደር ስርዓትን ሊያዘምን ይገባል ብለዋል፡፡

በቀጣይም ተቋሙ ለኦዲት ግኝቶቹ ትኩረት በመስጠት እንዲሁም በመድረኩ የተሰጡ አስተያየቶችንና ማሳሰቢያዎችን መሰረት ያደረገ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ የድርጊት መርሀ ግብርና የአፈጻጸም ሪፖርት በአጭር ጊዜ ውስጥ አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ አሳስበዋል፡፡

ጉዳዩ የሚመለከታቸው የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በሚመለከታቸው ጉዳዮች ዙሪያ አስፈላጊውን ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር እንዲያደርጉ ያሳሰቡት የተከበሩ አቶ ክርስቲያን በአሰራርና በአመራር መጓደል ለተፈጠረው የሀብት ብክነት ምክንያት የሆኑ እንዲሁም የወንጀልና የፍትሀብሔር ተጠያቂነት በሚያስከትሉ ጉዳዮች ላይ የፍትህ ሚኒስቴር ክስ እንዲመሰርት አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *