የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የምርምር በጀት አስተዳደር ስርዓትን አስመልክቶ በ2012/2013 በጀት ዓመት ባካሄደው የክዋኔ ኦዲት መሠረት የተሰጡ የማሻሻያ ሀሳቦች መተግበራቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል የመስክ ምልከታ ተካሄደ፡፡
የመስክ ምልከታው የተካሄደው በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የሰው ሀብት ስምሪትና ቴክኖሎጂ ቋሚ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲው የምርምር ፈንድ አስተዳደር ስርዓት ግልጽነት የጎደለው፣ ለምርምር የተመደበው በጀት ተግባራዊነትም ምቹ ያልሆነ፣ የተናበበና የተጣጣመ የተመራማሪዎች ትስስር እንዲሁም ከሌሎች የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች ጋር መፈጠር ያለበት የቅንጅት አሠራር ዝቅተኛ የሆነና ሴት ተማራማሪዎችን ከማብቃት ጋር ተያይዞም ክፍተት የነበረበት መሆኑ በ2012/2013 በጀት ዓመት በተካሄደው የክዋኔ ኦዲት መታየቱን ቋሚ ኮሚቴው አስታውሷል፡፡
የመስክ ምልከታው በኦዲቱ ወቅት የታዩ ግኝቶችን መሰረት በማድረግ ከመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትና ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ቀደም ሲል በተሰጡ የማሻሻያ ሀሳቦችና አቅጣጫዎች መሰረት ግኝቶቹን ለማስተካከል የተወሰዱ እርምጃዎችን ለማረጋገጥ የተካሄደ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው አመራሮች በተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች ዙሪያ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕ/ር ጣሰው ወልደሃና በማብራሪያቸው መንግስት ለዩኒቨርሲቲው የምርምር ስራ በጀት መመደቡ ጥሩ ቢሆንም ነገር ግን መመሪያው ከዩኒቨርሲቲው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አብሮ የማይሄድና የማያሰራ ሰለሆነ በዩኒቨርሲቲው አሠራር ላይ ጫና እየፈጠረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ምትኬ ሞላ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የኦዲት ግኝቶቹንና የተሰጡ አቅጣጫዎችን መሰረት አድርጎ የተለያዩ ማሻሻያዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው ኦዲቱን እንደ ስጋት ሳይሆን እንደ ትልቅ እድል እንደሚመለከተውና ክፍተቶቹንም መለየት እንዳስቻለው ገልጸዋል፡፡
የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ ማብራሪያውን ተከትሎ በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኦዲቱ ወቅት ያገኛቸውን የአሰራር ስርዓት ክፍተቶችና ጉድለቶች በተሰጡ አቅጣጫዎች መሰረት ለማስተካከል የሄደበትን ርቀት የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመው ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በላይ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የልማትና ማህበራዊ ተቋማት ክዋኔ ኦዲት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጳውሎስ ዘሪሁን በበኩላቸው መ/ቤታቸው በየጊዜው የክትትልና የቁጥጥር ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸው አሁንም ቢሆን የተወሰኑ ችግሮች ያለመቀረፋቸውንና ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ትኩረት ስጥቶ ሊሰራባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ ዩኒቨርሲቲው በምርምር ዘርፍ ከግል ባለሀብቶች እና ከኢንዱስትሪዎች ጋር ተቀናጅቶ ከመስራት አኳያ የተሻለ ጥረት እንዲያደርግ፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ያለውን የጋራ ስራ ትስስርም እንዲያጠናክር እና ሴት ተመራማሪዎች ከማብቃት አንጻርም የበለጠ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡
በመስክ ምልከታው ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዚክስ፣ ህዋ ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋም ጉብኝት ተካሂዷል፡፡