በፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ የተመራው ልዑክ የተሳተፉበትና ከጥቅምት 28 አስከ ህዳር 2 /2015 ዓ.ም በብራዚሏ ሪዮ ዲ ጀነሪዮ ከተማ በደቡብ አሜሪካ ኮንቬሽን ማዕከል ሲካሄድ የነበረው 24ኛው ዓለም አቀፍ የኦዲት ተቋማት ጉባኤ (INCOSAI) የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍና የአቻ ኦዲት ተቋማት የጎንዮሽ ውይይቶችን በማስተናገድ ተጠናቋል፡፡
ዓለም አቀፉ የኦዲት ተቀማት ጉባኤው በቆይታው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት የኦዲት ስራን ዓለምአቀፋዊ በሆነ ስታንዳርድ የበለጠ ለማጎልበት በሚያስችሉ የጋራ ጉዳዮች ላይ መክሯል፡፡
ጉባኤው የዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ሙስናን ለማጋለጥ በሚያደርጉት ጥረት በየሀገሮቻቸው ከሚገኙ ጸረ-ሙስና ተቋማት ጋር በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ አጽዕኖት ሰጥቶ የተወያየ ሲሆን በዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን /Global Expertise Team/ የተዘጋጀ ለዚህ የሚረዳ የአሠራር መመሪያም በጉባኤው ላይ ጸድቆ ቡድኑ መመሪያውን ለዓለም አቀፉ የኦዲት ተቋም (INTOSAI) አስረክቧል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤም ይህንን መመሪያ ከአዘጋጀው አካል የተረከቡ ሲሆን መ/ቤታቸው መመሪያውን ከሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ለመተግበር እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት 3 ዓመታት በ INCOSAI እና በአከባቢያዊ የኦዲት ማህበሮች /Regional Auditor General Organizations/ የተከናወኑ ስራዎችን የተመለከተ ሪፖርት በጉባኤው ላይ ውይይት ተደርጎበት የጸደቀ ሲሆን በተለይም የኮቪድ ወረርሽኝ የነበረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ እንደነበረ ተነስቷል፡፡
የዓለም አቀፍ የኦዲት ተቋማት ከ2022 እስከ 2028 የሚቆይ ስትራቴጂክ ዕቅድም ለጉባኤው ቀርቦ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል፡፡ ላለፉት 3 ዓመታት በትብብር የሠሩ አጋር አካላትም ሪፖርቶቻቸውን በጉባኤው ላይ ያቀረቡ ሲሆን በቀጣይም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡
በጉባኤው ወቅት የተለያዩ የጎንዮሽ ውይይቶች የተካሄዱ ሲሆን ክብርት ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው በተለያዩ አቻ የኦዲት ተቋማት የመ/ቤቱን አቅም ለማጠናከር እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ በሚችሉበትና በጋራ ትብብሮች ሁኔታ ላይ ከስዊዲን፣ ከቻይና፣ ከህንድ፣ ከብራዚል፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከኬኒያና ከሌሎችም ሀገራት የዋና ኦዲተር ኃላፊዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን አካሂደዋል፡፡
በተለይም ከስውዲን ዋና ኦዲተር መ/ቤት ኃላፊ ጋር በሁለቱ ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች መካከል ሊኖሩ ስለሚገቡ የትብብር ስራዎችና ድጋፎች ዙሪያ ውይይት ያደረጉ ሲሆን በተመሳሳይም ከህንድ ዋና ኦዲተር የልዑካን ቡድን ጋር የህንድ ዋና ኦዲተር ለመ/ቤቱ እያደረገ ያለውን የአቅም ግንባታ ድጋፍ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
የህንድ ዋና ኦዲተር በክዋኔ ኦዲት ዙሪያ በየዓመቱ እያደረገ ስላለው የወርክ ሾፕ አቅም ግንባታ ድጋፍ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ክብርት ዋና ኦዲተሯ መርሀ ግብሩ ለመ/ቤቱ አሠራር ጠቃሚ በመሆኑ እንዲቀጥል የጠየቁ ሲሆን የህንድ ዋና ኦዲተር ተቋም ዋና ኦዲተር ጊሪሽ ቻንድራ ሙሩሙ በበኩላቸው በሁለቱ አቻ ኦዲት ተቋማት መካከል ያለው የእርስ በእርስ መደጋገፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ክብርት ዋና ኦዲተሯ ከህዝባዊ ሪፐብሊክ ቻይና ብሔራዊ ኦዲት መ/ቤት ኃላፊ ዚንግ ጂያንፊንግ ጋር ባደረጉት ውይይት ቀደም ብለው በተደረጉ የሁለትዮሽ ስምምነት መሠረት በህዝባዊ ሪፐብሊክ ቻይና ብሔራዊ ኦዲት መ/ቤት በኩል እ.አ.አ ከ2020 ጀምሮ ለመ/ቤቱ ኦዲተሮች እየተሰጡ ያሉ የረጅም ጊዜ የትምህርት ዕድሎችን ጨምሮ እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች እንዲቀጥሉ የጠየቁ ሲሆን ኃላፊው በበኩላቸው ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡
በተለያዩ የጉባኤው አባል ሀገራት አዘጋጅነት በየሶስት ዓመቱ በሚካሄደውና በብራዚል አዘጋጅነት በተካሄደው የ2022 ቱ 24ኛው ዓለም አቀፍ የኦዲት ተቋማት ጉባኤ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የተወከለችውን ኢትየጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ የ147 ሀገራትና የ30 ተቋማት ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን ከ63 ዓመታት በፊት እ.አ.አ በ1959 የተካሄደውን 3ኛውን ጉባኤም የአሁኑ ጉባኤ አዘጋጇ ብራዚል ማዘጋጀቷ ታውቋል፡፡