የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ሚኒስቴር የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ አፈፃፀምን በተመለከተ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ያከናወነውን የክዋኔ ኦዲት መሰረት በማድረግ ይፋዊ ስብሰባ መጋቢት 24፣ 2010 ዓ.ም ባካሔደበት ወቅት የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ አፈፃፀም በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ አለመሆኑን ገለፀ፡፡
በይፋዊ ስብሰባው ቋሚ ኮሚቴው የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ሚኒስቴር በአዋጅ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት ውጤታማ፣ ቀልጣፋ እና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ከመተግባር አኳያ ውጤታማ ሊሆን ያልተቻለበትን ምክንያት የተቋሙ ኃላፊዎች እንዲያስረዱ የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርቧል፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤቱ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ለልማታዊ አገልግሎትና ለኢኮኖሚ ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዲያበረክት በዋነኛነት የሚያስፈልገውን ፖሊሲና ስትራቴጂ ያላዘጋጀ መሆኑ፤ ከውጭ አገር የሚገቡ የእንስሳት ዝርያዎች የዓለም አቀፍ የእንስሳት ጤና ድርጅት ያስቀመጣቸውን 6 የምርመራ መስፈርቶችን ሳያሟሉ በ2005 ከኔዘርላንድ አገር ላሞች መገዛታቸውንና የተገዙትም ላሞች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የበሽታ ምልክት ያሳዩና ውርጃ የታየባቸው እንዲሁም የተሰጠው ሰርተፍኬት የእንስሳቱን የጤና ሁኔታ የማይገልፅ መሆኑ፤ የድራት ማጎልበቻ ሆርሞን (በሲንክሮናይዜሽን ሰርቪስ) የተዳቀሉት እንስሳት ውጤት ወደ እርግዝና መለወጥና ጥጃ ወይም ጊደር የመውለድ ምጣኔ ዝቅተኛ እንደሆነና በዚህም ምክንያት በተጠቃሚው ዘንድ ቅሬታዎችን እያስነሳና በአርሶ አደሩ፣ በከፊል አርብቶ አደሩና አርብቶአደሩ ቴክኖሎጂውን እስከ መጠራጠር የተደረሰበት ሁኔታ መኖሩ፤ በእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ አጠቃቀምና ጥበቃ ላይ ለተሰማሩ ባለሃብቶች፣ ቡድኖችና የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽነትን ለማረጋገጥና ለማሻሻል፣ በኋላቀርና በዘልማድ ዝርያን የማሻሻልን ሂደት ለማስቀረት በፕሮግራም የዕውቀት ክህሎትና አቅም ግንባታ ሥልጠናዎች እንዲያገኙ አለመደረጉ እና ውጤታማና ቀልጣፋ የዝርያ ማሻሻያ ሥራን ለማከናወን ሚኒስቴር መ/ቤቱ ባለድርሻ አካላት ከሆኑት ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምርና ከከፍተኛ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ እንደማይሰራ ቋሚ ኮሚቴው ገልጾ ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጥባቸው የተቋሙን ኃላፊዎች ጠይቋል፡፡
ዶ/ር ገ/እግዚአብሔር ገ/ዮሃንስ በእንስሳት ዓሣ ሃብት ሚኒስቴር ዲኤታ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የእንስሳት ርቢ ፖሊሲና ስትራቴጂ በተመለከተ ፖሊሲውንና ስትራቴጂውን በማዘጋጀት ሂደት ላይ ረጅም ጊዜ መውሰዱና አስታውሰው በአሁኑ ሰዓት ዝግጅቱ ተጠናቆ በህትመት ታትሞ መውጣቱን፣ ፖሊሲውን ለማስፈፀም የሚያገለግሉ አዋጅና መመሪያ ማርቀቅ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ፣ የተቋሙን አደረጃጀት በማሻሻልም ብሔራዊ የሰው ሰራሽ ማራቢያ የነበረውን ወደ ኢንስቲትዩት ደረጃ እንዲያድግ መደረጉንና የማራቢያ ፕሮግራሞች እየተቀረፁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከውጭ አገር የገቡ የዝርያ ማሻሻያ ጊደር ላሞችን በተመለከተ የግብርና ሚኒስቴር እንስሳትንም ሆነ የእንስሳት ዘር ከውጭ አገር ሲያስገባም ሆነ ወደ ውጭ ሲልክ የሚመራበት መመሪያ እንዳለውና በመሥፈርቱም እንስሳቱን ከውጭ አገር ሲያስመጣ ከጤናና ከዝርያ አንፃር ግምገማ በማድረግ እንደሆነ ገልፀው በ2005 የገቡት ላሞችም ይህን መስፈርት ተከትለው መግባታቸውን ገልጸው ነገር ግን ላሞቹ ከገቡ በኋላ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች አገሮች የሚታወቅ አይ ቢ አር (IBR) በተባለ በሽታ ተጠቂ እንደነበሩና ክትባትም ሊሰጣቸው እንዳልተቻለ እንዲሁም ከነሱ የተወለዱትና ለአባለዘር ማምረት አገልግሎት ይውላሉ ተብሎ የታሰቡት ኮርማዎችም የአባላዘር በሽታው ሊተላለፍባቸው እንደሚችል ሲታወቅ በሥጋ መልክ እንዲወገዱ መደረጉን ዶ/ር ገ/እግዚአብሔር አስረድተዋል፡፡
የድራት ማጎልበቻ ሆርሞን በተመለከተም ዶ/ር ገ/እግዚአብሔር ሲመልሱ በኦዲት ግኝቱ የተገለፀው ትክክለኛ መሆኑንና ሰው ሰራሽ ማዳቀያ ሥራ ሲጀመር ውጤታማ እንደነበረ ገልፀው በሂደት ሥራው እየሰፋ ሲሄድ ከባለሙያ ክህሎት ማነስና ከግብዓት ውስንነት የተነሳ በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ ሊሆን እንዳልተቻለ አስረድተው በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል አጠቃቀምና ጥበቃ ላይ ለተሰማሩ ባለሃብቶች፣ ቡድኖችና የህብረተሰብ ክፍሎች ሥልጠና እንዲያገኙ ከማደረግ አኳያ ከተቋሙ ዋና የሥልጠና ማዕከል በተጨማሪ በአራት ክልሎች በሚገኙ የሥልጠና ተቋማት ውስጥ ሥልጠናውን ለማግኘት በርካታ ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች ቢኖሩም ለአንድ ባለሙያ የሚያስፈልገው ግብዓት እስከ 200 ሺህ ብር የሚጠይቅ በመሆኑ አቅሙ ኖሯው ግብዓቶቹን ገዝተው ወደሥራው የሚገቡ ሙያተኞች ውስን መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ባለድርሻ አካላትን አቀናጅቶ ከመስራት አንፃርም ሚንስትር መ/ቤቱ ውስንነት እንዳለበትና ያንንም ለማሻሻል የተለያዩ የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት ስትራቴጂዎች ሲቀረፁም ሆነ ሲተገበሩ በማሳተፍ ለመሥራት ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ሚኒስቴር በሰጡት ተጨማሪ ምላሽ የኦዲት ግኝቱ ጠቃሚ መሆኑን ገልፀው ከኦዲቱ አኳያ የማሻሻያ ሥራዎችን እየተሠሩ እንደሚገኙና በሂደት ውጤቱ እንደሚታይ፤ አቅም የሚጠይቁ ነገሮችን ለማስተካከል የስልጠና ስትራቴጂ እንደሚያስፈልግ በመገንዘብ የሥልጣና ተቋም መገንባት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኙ እና የእንስሳት ማዳቀያ ባለሙያዎች ከመደበኛ የሥራ ሰዓት ውጪ የሚሠሩበት ሁኔታ ስላለ ከሥራ ሰዓት ውጪ ለሚሠሩት ሥራ ተገቢውን ክፍያ መክፈል ያስችል ዘንድ መመሪያ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ የፌዴራል ዋና ኦዲተር በሰጡት አስተያየት ዝርያን ከማሻሻል አኳያ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ብዙ እንደሚቀራቸው፤ የአገራችን የእንስሳት ዝርያ በማሻሻል የተሻለ ምርትና ምርታማነት የሚገኝበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ፤ የዝርያ ማሻሻያ ሥራዎች ለውጥ ማምጣት ያልቻሉበት ምክንያት በአግባቡ ሊጠና እንደሚገባ፤ መንግስትንም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላትን በማሳተፍ በፍጥነት ለውጥ ማምጣት በሚያስችል አግባብ መንቀሳቀስ እንደሚገባ፤ ከውጭ የሚመጡ ዝርያዎችን በተመለከተም 6 የዓለም አቀፍ የእንስሳት ጤና ድርጅት መስፈርቶች ማሟላታቸው ተረጋግጦ መግባት ሲኖርባቸው መስፈርቶቹ አለመረጋገጣቸውንና ከነዚህም ውስጥ አንዱ አይ ቢ አር መሆኑንና ለዝርያ ከገቡት ላሞች የተወለዱት ኮርማዎችም የመተንፈሻ አካል ችግር ያለባቸው መሆኑ እየታወቀ ሲሰራጩ እንደነበረና ባለሙያዎቹም ተጠያቂ አለመደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
የአባላዘር አቅርቦትን በተመለከተም ፍላጎቱ ብዙ ቢሆንም አቅርቦቱ ትንሽ እንደሆነና አቅርቦቱ በሚሻሻልበት ሁኔታ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ፤ ከድራት ማጎልበቻ ሆርሞን ጋር በተያያዘም ለእንስሳቱ የሚሠጡት መድሃኒቶች ትክክለኛነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ፤ ከአቅም ግንባታ ጋር በተያያዘ ብዙ ሥራ እንዳልተሰራ ታውቆ የአገር በቀል ምርጥ ልምዶችን የመጠቀም ሁኔታ ሊጎለብት እንደሚገባ እና ሚኒስቴር መ/ቤቱ በኦዲት ግኝቱ ከተመላከቱት ችግሮች ውጪ አስፍቶ በመመልከት በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አቶ ገመቹ አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ት ወይንሸት ገለሶ በመጨረሻ በሰጡት አስተያየት የኦዲት ግኝቶችን መሠረት በማድረግ ምቹ ሁኔታ በዘርፉ እየዘረጉ መሄድ እንደሚያስፈልግ፤ ፖሊስና ስትራቴጂ በዘርፉ ከሌለ ለተጠያቂነትም ሆነ ሥራውን ለማከናወን አስቸጋሪ ስለሚያደርገው በተጀመረው መንገድ በፍጥነት ወደተግባር መለወጥ እንደሚያስፈልግ፤ በዘርፉ ይበልጥ ትኩረትና ቅድሚያ ተሰጥቶ ሊሠራባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በመለየት በተቀናጀ እቅድ ሊመራ እንደሚገባ፤ ከውጭ አገር በሚመጡ እንስሳት ላይ ተገቢው ትኩረት ሊሰጥና ተጠያቂነት የሚያረጋግጥ ሥርዓት ሊበጅለት እንደሚገባ፤ የውስጥ አቅምን ከመገንባት በተለይም የባለሙያ እጥረትን ከመቅረፍ አንፃር ከክልሎች ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግ፤ በዘርፉ ለተሠማሩ ባለሃብቶችና አርሶ አደሮች ምቹ የሥራ ሁኔታ ሊፈጠርላቸው እንደሚገባ፤ በአገር ውስጥ ምርታቸው ጥሩ የሆኑ የእንስሳት ዝርያዎችን በመለየትና ቅድሚያ በመስጠት ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ፤ ቅንጅታዊ አሠራርን ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፤ ከክልሎችና ከሌሎች ባለድረሻ አካላት ጋር ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ እንዲሁም ሚኒስቴር መ/ቤቱ በኦዲት አስተያየቱ መሠረት የሚወሰዱ እርምጃዎችን ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቅ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡
በሚኒስቴር መ/ቤቱ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ አፈፃፀም ውጤታማ አለመሆኑ ተገለፀ
