News

ቋሚ ኮሚቴዎች የኦዲት ግኝትን ለክትትልና ቁጥጥር ሥራቸው አጋዥ መሣሪያ አድርገው ሊሠሩ እንደሚገባ ተገለጸ

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሉ የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች የኦዲት ግኝትን ለክትትልና ቁጥጥር ሥራቸው አጋዥ መሣሪያ አድርገው ሊሠሩ እንደሚገባ የምክርቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሜቴ ገለጸ፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በቢሾፍቱ ከተማ ለምክር ቤቱ የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና ምክትል ሰብሳቢዎች፣ ለመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት እና ሌሎች የኦዲት ባለድርሻ አካላት ከጥር 28-29/2015 ዓ.ም ለሁለት ቀናት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

በመድረኩ ማጠቃለያ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩን ሌሎች የኦዲት ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ላዘጋጀው የፌደራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እንዲሁም ለቁጥጥር ሥራ የጋራ በሆነው መድረክ በመገኘት ንቁ ተሳትፎ ላደረጉት የምክርቤቱ አባላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴዎች የዲሞክራሲ ተቋማት እንዲጠናከሩ በማገዝ የተጣለባቸውን ትልቅ ኃላፊነት እንዲወጡ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም አስፈጻሚ አካላት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ሲያቀርቡ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ ስለመውሰዳቸው በሪፖርታቸው ማከተታቸውን መከታተል እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ጥራትን ከማሳደግ ባለፈ የኦዲት ሥራ ፋይዳን በሚመለከት በየጊዜው የህብረተሰቡን እና የኦዲት ተደራጊ ተቋማትን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች በሰፊው ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ለመድረኩ ውጤታማነት የበኩላቸውን ገለጻ በማቅረብ የተሳተፉትን የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ የመንግስት ግዢና ንብረት ባለሥልጣን እንዲሁም የስነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽንን አመስግነዋል፡፡

በመድረኩ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ የተለያዩ ኦዲት ነክ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትን ጨምሮ ሌሎች የዲሞክራሲ ተቋማትን ነጻና ገለልተኛ ሆነው እንዲደረጁ ማድረግ ምክር ቤቱ የሚያደርገውን የክትትልና የቁጥጥር ሥራ ከማገዝ ባለፈ የጸና መንግስት እንዲኖር ያስችላል ብለዋል፡፡

በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ለፓርላማው የክትትልና ቁጥጥር ተግባር ጉልህ ሚና ያላቸው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን እንዲሁም የመንግስት ግዢና ንብረት ባለስልጣን ተቋማት ከኦዲት አኳያ ገለጻ ከማቅረብ ባለፈ በመድረኩ ለተነሱ ጥያቄዎችም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *