News

ቋሚ ኮሚቴው ይፋዊ ህዝባዊ ስብስባ አካሄደ

የ ኢ. ፌ. ዴ. ሪ. የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2012/2013 በጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የግል 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶችን አስመልክቶ በትምህርት ሚኒስቴር ላይ ያካሄደውን የክዋኔ ኦዲት መሰረት ያደረገ ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ ታህሳስ 25 ቀን 2014 ዓ.ም አካሄደ ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በናሙና በተመረጡ  የግል 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የተካሄደውን  የክዋኔ ኦዲት ተከትሎ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለሚኒስቴር መ/ቤቱ የተሰጡ የማሻሻያ ሀሳቦችን መሰረት ያደረጉ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ለማረጋገጥ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በተካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ የቋሚ ኮሚቴው አባላት፣ የሰው ሀብትና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የስራ ኃላፊዎች፣ የትምህርት ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች የባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

በኦዲት ግኝቱ መሰረት የታዩ ክፍተቶችን አስመልክቶ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ምላሽ እንዲሰጡባቸው በቋሚ ኮሚቴው ዝርዝር ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ የግል ት/ቤቶች ፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር መመሪያ የቆየና ያልተሻሻለ በመሆኑ የፈቃድ አሰጣጥና እድሳትን የተመለከተ የተሻሻለ መመሪያና ስታንዳርድ የሌለ  ስለመሆኑ፣ የማህበረሰብ ት/ቤቶችን (Community Schools) እና የኣለም አቀፍ ት/ቤቶችን ( International Schools) ለይቶ ለመመደብ የሚያስችል የፈቃድ አሰጣጥና እድሳት ቼክ ሊስት የሌለና በእነዚህ ት/ቤቶችም የውጭ አገር መምህራንን የስራ ፈቃድ አሰጣጥ ጨምሮ ወጥ የሆነ አሠራር የሌለ ስለመሆኑ ለሚኒስቴር መ/ቤቱ የተሰጡ የማሻሻያ ሀሳቦች ተግባራዊ ስለመሆናቸው ጥያቄ ቀርቧል፡፡

በተጨማሪም የት/ቤቶቹን ግንባታና ግብአት አስመልክቶ የት/ቤቶቹን ማሀበረሰብ ከአደጋ ለመጠበቅ የሚያስችሉ መከላከያዎች መስፈርታቸውን አሟልተው ያልተገኙ ስለመሆናቸው እና የተወሰኑት ት/ቤቶችም መሰረታዊ የትምህርት ግብአቶችና ሊኖራቸው የሚገባውን የቦታ ስፋት ያላሟሉና በአካባቢያቸው ለትምህርት ስራ የማይመቹ አዋኪ ነገሮች ያሉባቸው ስለመሆናቸው እንዲሁም  አብዛኞቹ ዝቅተኛውን የትምህርት ስታንዳርድ የማያሟሉ መሆኑን አስመልክቶ በተሰጠው የማሻሻያ ሀሳብ መሰረት እርምጃ ስለመወሰዱ በቋሚ ኮሚቴው ተጠይቋል፡፡

አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች የልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች ምቹ ያለመሆናቸውና ለእነዚህ ተማሪዎች የሚያስፈልጉ ልዩ ግብአቶችና ብቁ የሆኑና በሙያ ብቃት ምዘናና በተከታታይ ሙያ ማሻሻያ መርሀ ግብሮች ውስጥ ያለፉ ርዕሳነ መምህራንና መምህራንን ጨምሮ በልዩ ፍላጎትና በምክርና ድጋፍ ትምህርት የሰለጠኑ ባለሙያዎች ያልተሟሉ ስለመሆናቸው እንዲሁም የሙያ ፈቃድ አሰጣጥ ሂደትና አተገባበሩን በበላይነት የሚያስተባብረው ሀገር አቀፍ ካውንስል በመመሪያው መሰረት ምንም ስራ ያልሰራና በሚኒስቴር መ/ቤቱ እየተከናወነ ያለው የዳታ ቤዝ ግንባታና ትግበራም በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ ያለመሆኑን አስመልክቶም  የሚኒስቴር መ/ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ምላሽ እንዲሰጡ ጥያቄ ቀርቧል፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩን ክቡር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ በስብስባው ላይ የተገኙ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ለቀረቡት ዝርዝር  ጥያቄዎች  ምላሽ የሰጡ ሲሆን  እንደ አጠቃላይ የሀገሪቱ የትምህርት ዘርፍ በርካታ ችግሮች ያሉበትና በሀገሪቱ ካሉ ትምህርት ቤቶች 90% የሚሆኑት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ስታንዳርድ የማያሟሉ በመሆናቸው ከችግሩ ግዝፈት አንጻር ለመፍትሔው የህዝብ ተወካዮች ም/ቤትን ጨምሮ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን በመጠቆም የኦዲት ግኝቶቹ ለሚኒስቴር መ/ቤቱ ቀጣይ አሠራር መነሻ የሚሆኑ ጠቃሚ ግብአት መሆናቸውን በመግቢያቸው ላይ አንስተዋል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር በአዋጅ የተሰጠውን የሀገሪቱን የትምህርት ስታንዳርድ የማውጣትና ለአለም አቀፍና የማህበረሰብ ትምህርት ቤቶች ፈቃድ የመስጠት ስልጣንና ኃላፊነትን ከክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች አተገባበር ጋር ለማጣጣም ሰፊ ሀገራዊ የጋራ ስራ የሚጠይቅ መሆኑን ያመላከቱት አመራሮቹ  የትምህርት አዋጁ  ባለመጽደቁ በረቂቅ ደረጃ ተዘጋጅቶ  ያለውን የግል ትምህርት ቤቶች ፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር ደንብ ማውጣትና መተግበር እንዳልተቻለ በምላሻቸው ጠቅሰዋል፡፡

የመምህራን የሙያ ብቃት ምዘናን በተመለከተ ስራው በፕሮጀክት ሲሰራ የነበረና በመንግስት በጀት የሚከናወን ስላልነበር ፕሮጀክቱ ሲቆም ስራው እንደተቋረጠ የጠቀሱት የሚኒስቴር መ/ቤቱ አመራሮች በአሁኑ ሰዓት በተወሰኑ የግል ት/ቤቶች የምዘናውን ስራ መተግበር መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡ የሙያ ፈቃድ አሰጣጥ አጠቃላይ ሂደቱንና አተገባበሩን በበላይነት የሚያስተባብር አገር አቀፍ ካውንስል ተቋቁሞ ወደ ስራ ለመግባት ቢዘጋጅም አዲስ የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን የማቋቋም ሂደቱን ተከትሎ የካውንስሉ ተጠሪነት ለማን እንደሆነ ባለመታወቁ ካውንስሉን እስካሁን ወደስራ ማስጋባት ያለመቻሉንና ተጠሪነቱ እንደታወቀ ወደ ስራ እንደሚገባም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የመረጃ ዳታ ቤዝ ግንባታና ትግበራን በተመለከተ የኢንስፔክሽን መረጃ መያዣ ዳታ ቤዙ ተጠናቆ ወደ ስራ የተገባ መሆኑንና የሙያ ብቃት ምዘና ውጤት መያዣውንም ለመተግበር የሚያስችል ስልጠና ለክልሎች ተሰጥቶ  መደስራ ለመግባት የሚያስችል ሂደት ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የትምህርት ቤቶቹን ማህበረሰብ ከተለያዩ አደጋዎች ለመጠበቅ ሊወሰድ በሚገባው ቅድመ ጥንቃቄ ላይ የታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል  በሱፐርቪዥንና ኢንስፔክሽን ስራዎች ችግሮቹን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የጠቀሱት አመራሮቹ በት/ቤቶች አካባቢ የሚታዩ አዋኪ ነገሮችን ከትምህርት ቤቶቹ አካባቢ ጨርሶ ለማስወገድ  ጉዳዩ የሌሎች ባለድርሻ አካላትን ትብብርና ውሳኔ የሚጠይቅ ሆኖ በመገኘቱ ችግሩን  ሙሉ በሙሉ ማስወገድ እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡

የልዩ ፍላጎት ተጠቃሚ ተማሪዎችን ለመርዳትና ለማገዝ እንዲቻል ትምህርት ቤቶች ለአካል ጉዳተኞች የሚሆኑ የተለያዩ አስፈላጊ ግብአቶችን ማሟላት የሚገባቸው መሆኑን የጠቀሱት አመራሮቹ በተለያዩዩ የክትትል ዘዴዎች ግብአቶቹ መሟላታቸውን የማረጋገጥ ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዉ በልዩ ፍላጎትና በምክርና ድጋፍ አገልግሎት ሙያ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን እንደልብ በገበያ ላይ ማግኘት ባለመቻሉ  ክፍተቱ ያለ ቢሆንም ለሌሎች መምህራን አጫጭር ስልጠናዎችን በማዘጋጀት ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ በመድረኩ የተጋበዙ የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በኦዲት ማሻሻያ ሀሳቦች እርምጃ አወሳሰድ ላይ ከሚኒስቴር መ/ቤቱ አመራሮች የተሰጡ ምላሾችን መሰረት በማድረግ አስተያየቶችን  ሰጥተዋል፡፡

የትምህርት ዘርፍ የሀገሪቱን ዜጎች ለመቅረጽ ወሳኝ ሚና የሚጫወት እንደመሆኑ በፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር፣ በመምህራን ልማት፣  ምዘናና ሙያዊ ፈቃድ፣ የልዩ ፍላጎትና ሌሎች ግብአቶችን በማሟላት እና የመረጃ ዳታ ቤዙን ግንባታና አተገባበር ውጤታማ በማድረግ ረገድ እንዲሁም ትምህርት ቤቶቹን ጤናማ የትምህርት ተቋም ከማድረግ አንጻር ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው በመሆኑ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በኦዲቱ ግኝት መሰረት የተሰጡ የማሻሻያ ሀሳቦችን በድርጊት መርሀ ግብር እና በእቅድ ውስጥ አካቶ መተግበር እንደሚገባው በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡

ችግሮቹን ከፖሊሲና መመሪያዎች ያለመኖር ጋር ብቻ ማስተሳሰሩ ተገቢ ያለመሆኑንና የግል የትምህርት ተቋማት መንግስት በዘርፉ ያልሸፈናቸውን ክፍተቶች የሚሸፍኑ አጋር አካላት ተደርገው መታየት እንደሚኖርባቸው የጠቆሙት የቋሚ ኮሚቴዎቹ አባላትና ባለድርሻ አካላቱ አጠቃላይ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን በጥራት ማዕቀፍ በማካተት የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት አሳትፎ ቁርጠኝነት የታከለበት የትግበራና የቁጥጥር  ስራ መከናወን እንዳለበትና ትምህርት ቤቶቹም ፈቃድ ለማግኘት ዝቅተኛውን መስፈርት ማሟላት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ አክለውም ለትምህርት ጥራት ተብሎ ከዓለም ባንክ የተገኘውን የድጋፍ በጀት በአግባቡ በመጠቀም ስራዎችን በተጠያቂነት መንፈስ ማከናወን እንደሚገባ ጠቅሰው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የዚህን የድጋፍ በጀት አፈጻጸም በቀጣይ ኦዲት  መፈተሽ እንዳለበት  ጠቁመዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ም/ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው   በኦዲት ግኝቱ መሰረት የተሰጡትን የማሻሻያ ሀሳቦችና ከመድረኩ የተሰጡ አስተያየቶችን በመውሰድና  ይህንንም በድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅቶ በእቅድ በማካተት በታዩ ክፍተቶች ላይ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ የሚያስፈልግ መሆኑን አሳስበዋል፡፡

ኦዲቱ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በአዋጅ የተሰጡትን ስልጣንና ኃላፊነቶች መሠረት አድርጎ ከ2010 አስከ 2013 በጀት ዓመት የነበረውን አፈጻጸም የሸፈነ መሆኑን ያመላከቱት ክብርት ዋና ኦዲተሯ በወቅቱ በመላው ሀገሪቱ በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ  ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ በክልልና በከተማ መስተዳደሮች ያሉ ሌሎች የግል ት/ቤቶችን በናሙናነት ወስዶ  በኦዲቱ ማካተት ያለመቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

ሚኒስቴር መ/ቤቱ ደንቦችና መመሪያዎችን ወቅቱን ጠብቆ በማሻሻል የሙያ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓቱንም ሆነ የትምህርት ሂደቱን የመከታተልና የመቆጣጠር፣ የት/ቤቶቹ ግንባታዎች ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ጨምሮ ለተማሪዎችና ለት/ቤቶቹ ማህበረሰብ ምቹ፣ ከአዋኪ ነገሮች የጸዱና  ለአደጋ ያልተጋለጡ መሆኑን የማረጋገጥ፣ ለትምህርት ቤቶቹ የሚያስፈልጉ ግብአቶች መሟላታቸውን ክትትልና ቁጥጥር  አድርጎ እንዲስተካከሉ የማድረግ እንዲሁም  ብቁና የሙያ ማረጋገጫ ምዘና ወስደው ለትምህርቱ ስራ ተገቢ የትምህርት ዝግጅትና ዕውቀት ያላቸው ርዕሳነ መምህራን፣ መምህራንና ሌሎች ድጋፍ ሰጭ ባለሙያዎች መሟላታቸውንና በሙያ ማሻሻያ የተለያዩ መርሀ ግብሮች ውስጥ መካተታቸውን የማረጋገጥ ተግባር ማከናወን የሚገባው በመሆኑ በኦዲቱ የታዩ ክፍተቶችን ለማረምና ለማስተካከል ቀጣይ ጠንካራ ጥረት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡ የዳታ ቤዝ ግንባታና ትግበራን ጨምሮ የትምህርት ግብአቶችን ለሟሟላት የደንብና መመሪያ መኖር ግዴታ ያለመሆኑን የጠቆሙት ክብርት ም/ዋና ኦዲተሯ ህጉን የተከተለ የመንግስትን በጀት መጠቀም ሲቻል የሙያ ብቃት ምዘናና ሌሎች ስራዎችን ለመስራት ሁልጊዜ የፕሮጀክት በጀት መጠበቅ አግባብ ያለመሆኑን ጠቅሰው እስከ አሁን በትምህርት ዘርፍ በርካታ የኦዲት ስራዎች ተሰርተው እርምጃ መውሰድ የሚያስችሉ የማሻሻያ ሀሳቦች ቢሰጡም የሚጠበቀውን ያህል ውጤት ያለመገኘቱን አመላክተዋል ፡፡

በመጨረሻም የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከተለያዩ አካላት ከመድረኩ የተሰጡ ገንቢ ሀሳቦችን በመውሰድና በእቅድ ውስጥ በማካተት የኦዲት ግኝቶቹን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ውጤታማ ስራ ለመስራት መዘጋጀት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ሚኒስቴር መ/ቤቱ የሀገሪቱ የትምህርት ጉዳይ የመጨረሻው ውሳኔ ሰጪ አካል እንደመሆኑ በአዋጅ የተሰጡትን ስልጣንና ኃላፊነቶች በአግባቡ  ተጠቅሞ  ለረጅም ጊዜያት አብረውት የቆዩትን የትምህርት ስርዓት ሂደት ፣ የአሠራር፣ የፖሊሲና የስታንዳርድ  የግብአት እና ሌሎች ችግሮችን ለመቅረፍ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንደሚገባው አሳስበው ለአተገባበሩ መቃናት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *