News

ቀጣዩ ተግባር የኦዲት ግኝትን በማያርሙ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሆነ ተገለጸ

በኦዲት ግኝት ላይ ማስተካከያ በማያደርጉ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ ቀጣዩ ተግባር እንደሆነ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ገለጹ፡፡ ክቡር አቶ ገመቹ የፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶችን የ2010 በጀት አመት የሂሳብና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርትን ግንቦት 22፣ 2011 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል፡፡

ክቡር አቶ ገመቹ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2010 በጀት አቅራቢ ከነበሩት 182 የፌዴራል መንግስት ባለበጀት መ/ቤቶች መካከል 176 መ/ቤቶችንና 46 ቅርንጫፍ መ/ቤቶቻቸውን እንዲሁም የመንግስት አጠቃላይ ገቢና ወጪ ሂሳብ ኦዲትን በራሱ ኦዲት በማድረግ፤ ስድስት የሂሳብ ኦዲቶችን ደግሞ በሂሳብ ምርመራ ኮርፖሬሽን ኦዲት በማስደረግ የኦዲት ሽፋኑን እንደቀደሙት አመታት ሁሉ  100% ለማድረስ አቅዶ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ሆኖም አንድ ዩኒቨርስቲ በጸጥታ ችግር ኦዲት ባለመደረጉና ሌላ አንድ ዩኒቨርስቲ ደግሞ ሂሳቡን ዘግቶ ማስመርመር ባለመቻሉ 174 መ/ቤቶችና 46 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶቻቸውን እንዲሁም የመንግስት አጠቃላይ ገቢና ወጪ ሂሳብ ኦዲት ማድረጉንና  አፈጻጸሙም 98.87% ሊሆን መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በክዋኔ ኦዲት ረገድም 24 የክዋኔ ኦዲቶችንና 6 የክትትል ኦዲቶችን ለማከናወን ታቅዶ 23 የክዋኔ ኦዲቶች መጠናቀቃቸውንና አንደኛው ግን ተጀምሮ ሳይጠናቀቅ ወደ 2011/2012 የኦዲት ዘመን መሸጋገሩን ገልጸዋል፡፡ የክዋኔ ክትትል ኦዲቱም 5 መከናወኑንና አንደኛውን ማከናወን ሳይቻል መቅረቱን ገልጸዋል፡፡ ባጠቃላይም የክዋኔ ኦዲት የእቅድ አፈጻጸሙ 93.33% ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ሌላም የመሰረታዊ አገልግሎት ከለላ ኦዲትን በ264 ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በክልልና ዞን ደረጃ በሚገኙ ፈጻሚ ሴክተር ቢሮዎች ለማከናወን ታቅዶ በ231 ወረዳዎችና የከተማ አስተዳዶደሮች መከናወኑንና አፈጻጸሙም 87.5% መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አፈጻጸሙ የቀነሰውም በርካታ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ የልዩ ኦዲት ጥያቄዎች ከተለያዩ አካላት በመቅረባቸው የሰው ሀይል ወደነዚህ ኦዲቶች በመዛወሩ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ 11 ልዩ ኦዲቶችም ተጠናቀው ለጠያቂው አካል እንደተላኩ አክለዋል፡፡

ክቡር ዋና ኦዲተሩ በመ/ቤቱ የ2010 በጀት አመት የሂሳብ ኦዲት ከተደረገባቸው 174 ተቋማት ውስጥ 25 መ/ቤቶች ነቀፌታ የሌለባቸው መሆኑን፣ 89 ተቋማት ከጥቂት ጉድለት በስተቀር በአጠቃላይ አጥጋቢ ሆነው መገኘታቸውን፣ 11 ተቋማት የኦዲት አስተያየት ሊሰጥባቸው ያለተቻለ መሆኑን እና 49 ተቋማት የጎላ ችግር ያለባቸው በመሆኑ ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት የተሰጣቸው መሆኑን በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡

ክቡር አቶ ገመቹ በ2010 በጀት አመት የሂሳብ ኦዲት መሰረት አብዛኞቹ የኦዲት ተደራጊ ተቋማት ባለፉት አመታት የታዩትን የአሰራር ግድፈቶችን በማረምና የተዘረጋውን የመንግስት የፋይናንስ፣ የግዥና የንብረት አስተዳደር ስርአት ተጠቅመው በመስራት ረገድ በሚጠበቀው ልክ ለውጥ እያሳዩ አይደለም ብለዋል፡፡

በመሆኑም ለሂሳብ ኦዲት ግኝቶች ትኩረት ተሰጥቶ እርምጃ ሊወሰድባቸውና ሊስተካከሉ እንደሚገባ ገልጸው ይህንን ያላደረጉ ተቋማትም ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ተጠያቂ መደረግ አለባቸው ብለዋል፡፡ የክዋኔ ኦዲት ግኝቶቹ ላይም በምክር ቤቱ በኩል በጥልቀት ታይተውና ተመርምረው ተገቢው እርምጃ ሊወሰድ እንዲሁም ክትትልና ግፊት ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡

መጋቢት 16፣ 2011 ዓ.ም በምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ሰብሳቢነት ከኦዲት ተደራጊ ተቋማት ጋር በኦዲት እርምጃ አወሳሰድ ላይ ውይይት ተደርጎ በቀጣይ ሁለት ወራት ውስጥ ተቋማት የድርጊት መርሀ ግብር በማዘጋጀት እርምጃ ወስደው ለዋና ኦዲተርና ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቁ መወሰኑን ያስታወሱት ክቡር ዋና ኦዲተሩ ከተቋማቱ ውስጥ 27 ብቻ የድርጊት መርሀግብር መላካቸውንና አምስቱ ብቻ የወሰዱትን እርምጃ ማሳወቃቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም በውይይቱ ላይ የተወሰነውን ውሳኔ ባልፈጸሙት አካላት ላይ በወቅቱ በተወሰነው መሰረት ጠቅላይ አቃቤ ህግ እርምጃ ይወስዳል ተብሎ እንደሚጠበቅና ለዚህም አስፈላጊው ማስረጃ እንዳለው ገልፀዋል፡፡

ክቡር አቶ ገመቹ የምከር ቤቱ አባላት ላቀረቡዋቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት ተቋማት ከሀብት አስተዳደርና ተልዕኮ አፈጻጸም አኳያ የሚታይባቸውን ችግር ከአመት አመት በማያርሙበት ሁኔታ ውስጥ ምክር ቤቱ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሪፖርትን ብቻ ማዳመጡ በቂ ባለመሆኑ ለተግባራዊ እርምጃ ውሳኔ ላይ መድረስ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ለዚህም ተቋማት ከኦዲቱ አኳያ ስለሚገኙበት ሁኔታ ምክር ቤቱ ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ውይይት ማድረግ እንደሚያስፈልገው ጠይቋል፡፡

የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ የኦዲት ጉዳይን ለመከታተል በርሳቸው የሚመራ ልዩ ኮሚቴ በማዋቀር ምክር ቤቱ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው በተለይ ከአሰራርና ከህግ ማዕቀፍ ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮች ተለይተው መሰራቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህም በህግ ማዕቀፍ ዙርያ የመጡ ለውጦች እና አንዳንድ የተሻሻሉ ሁኔታዎች እንዳሉ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ክቡር አቶ ታገሰ ልዩ ኮሚቴው በኦዲት ተደራጊ ተቋማት ላይ መጋቢት 16፣ 2011 ዓ.ም ውይይት ባደረገበት ወቅት ሁሉም ተቋማት በኦዲት ግኝት ላይ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ እርምጃ ወስደው እንዲያሳውቁ ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸው ይህንን በማይተገብሩት ላይም የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ እርምጃ እንዲወስድ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡

ምክር ቤቱ ከዚህ በኋላ የኦዲት ሪፖርት እያደመጠ እንደማይቀጥል በአጽንዖት በመግለጽ የምክር ቤቱ አቋም በእዲት ሪፖርቱ መነሻነት ጠቅላይ አቃቤ ህግ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ በክዋኔ ኦዲት ላይም ሁሉም የምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች ክትትል ያደርጋሉ ብለዋል፡፡ በመጨረሻ በኦዲቱ ላይ መሰረት ያደረገ የምክር ቤቱ የጋራ ውሳኔ በቀጣይ ውይይት ተደርጎበት እንደሚጸድቅ የተከበሩ አፈ ጉባኤው ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *