News

ሚኒስቴር መ/ቤቱ በኦዲት ግኝቶች ላይ የሚወስደውን የእርምት እርምጃ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለጸ

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የ2015 በጀት ዓመት የሂሳብ ኦዲት ግኝቶችን ለማሻሻል እየወሰዳቸው ያሉ የእርምት እርምጃዎች አበረታች መሆናቸውንና  እርምጃዎቹን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ ገለጸ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ከባለድርሻ አካላት ጋር  መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የ2015 በጀት ዓመት የሂሳብ ኦዲት ግኝት ላይ ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ አካሂዷል፡፡

በኦዲት ግኝቱ የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ የተወራረደ የውጭ ጉዞ አበል መገኘቱ፣ በመመሪያው መሠረት ያልተመዘገቡ የግንባታ ሂሳቦች መኖራቸው፣ የመነሻ የምዝገባ ሰነድ ያልቀረበበት ተሰብሳቢ እና ተከፋይ ሂሳብ መገኘቱ፣ የእለት የተሰበሰቢ ገቢ ከ4 እስክ 130 ቀናት ቆይቶ ገቢ የሚደርግ መሆኑ፣ በወቅቱ ያልተወራረደ ውዝፍ ተሰብሳቢና ተከፋይ ሒሳቦች መገኘታቸው፣ በግልጽ ጨረታ መፈጸም የሚገባቸው ግዢዎች ያለውድድር በቀጥታ ግዢ ተፈጽመው መገኘታቸው እንዲሁም የተለያዩ ንብረቶችና ተሽከርካሪዎች አያያዝና አጠቃቀሞች የንብረት አስተዳደር መመሪያ ያልተከተሉ ሆነው መገኘታቸው  በመድረኩ ተጠቅሶ ግኝቶቹን ለማስተካከል የተሰሩ ሥራዎችን የሚኒስቴር መ/ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ እንዲሰጡ ቋሚ ኮሚቴው ጠይቋል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ  ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ጨምሮ በመድረኩ የተገኙ የተቋሙ አመራሮች የኦዲት ግኝቶቹን ትክክለኛነት ማረጋገጫ በመስጠትና ከኦዲቱ በኋላ መስተካከል የሚገባቸውን የመለየት ስራ መሰራቱን በመግለጽ በአብዛኞቹ የኦዲት ግኝቶች ላይ የማስተካከያ እርምጃ መውሰዱንና እና በቀጣይም የተጀመሩት የማስተካከያ እርምጃዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ተደሰ በበኩላቸው የኦዲት ግኝቶቹን ለማስተካከል ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን እና አብዛኞቹን ግኝቶች ማስተካከላቸውን ገልጸው በቀጣይ ከገቢ አሰባሰብ፣ ከበጀት አጠቃቀም እና ከንብረት አያያዝ ጋር ያሉና ያልተስተካሉ ቀሪ ሥራዎች ማስተካከል እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከኦዲት ግኝት ለመውጣት ያደረገውን ጥረት እና ኦዲቱ ካየው እይታ ውጪ ይበልጥ በተቋሙ ያሉ ችግሮችን በመመርመር ለማረም ስለተሰራው ስራ በማመስገን ከምዝገባ፣ ከእለት ገቢ አሰባሰብ፣ የግዢ ሥርዓት ተከትሎ ግዢዎችን ከመፈጸም እና ከበጀት አጠቃቀም ጋር አሁንም ያሉ ችግሮችን በአግባቡ መፈተሽና ማስተካከል እንደሚገባ ገልጸው በተለይ ከነዳጅ አጠቃቀም አንጻር ሚኒስቴር መ/ቤቱ ምሳሌ መሆን ያለበት በመሆኑ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ተከበሩ የሺእመቤት ደምሴ (ደ/ር) ሚኒስቴር መ/ቤቱ ኦዲቱን የጋራ በማድረግ ግኝቶቹን ለማሻሻል የሄደበትን ርቀት በአድናቆት የሚመለከቱት መሆኑን ገልጸው ኦዲቱ በናሙና ላይ ተመስርቶ የተሰራ በመሆኑ ይበልጥ አሰራራቸውን አስፍተው እንዲያዩ አሳስበዋል፡፡

አያይዘውም በቀጣይ ሠራተኞች ጋር የሚቆዩ ገቢ ሂሳቦችን በሰዓቱ ወደባንክ ገቢ ማድረግ የሚያስችል ሥርዓት እንዲያበጁ፣ ተግባራዊ የተደረገውን የኤሌክትሮኒክስ ግዢ ሥርዓት በአግባቡ ተፈጻሚ እንዲያደርጉ፣ ተሰብሳቢና ተከፋይ የቆዩ ሂሳቦች ማቆሚያ ሊበጁላቸው እንደሚገባና እና በተለይም ከንብረት አያያዝ ጋር በተገናኘ ያሉ ቀሪ ሥራዎች እንዲስተካከሉ አሳስበዋል፡፡

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *