የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሠራተኞች አጎራባች ከሆኑት የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ሠራተኞች ጋር በመሆን በመ/ቤቶቹ ቅጥር ግቢ 17ኛውን ብሔራዊ የሰንደቅ አላማ ቀን አክብረዋል፡፡
በአከባበር ስነስርዓቱ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሠ እንዲሁም ሌሎች አመራሮችና ሠራተኞች የተገኙ ሲሆን የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ( ዶ.ር) በስነስርኣቱ ላይ በመገኘት የአከባበር አላማውን አስመልክቶ አጭር ንግግር አድርገዋል፡፡
የሀገሪቱ ብሔራዊ ሰንደቅ አላማ የሀገሪቱን ሁለ ገብ እንቅስቃሴ ለማሳካት መሠረት የሆነውን የመላ ሀገሪቱን ህዝቦች አንድነት ጠብቆ ለማቆየት አስፈላጊ መሆኑን በንግግራቸው የጠቀሱት ክቡር ኮሚሽነሩ ለሀገር ሰላም፣ አንድነት፣ ብልጽግና እና ለሀገሪቱ እድገት ጸንቶ መቆም ሁሉም ሰው በተሰማራበት ሙያ የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይገባዋል ብለዋል፡፡
በስነስርኣቱ ላይ በአካባቢው በሚገኙ የፌዴራል ፖሊስ አባላት የሰልፍ ስነስርዓት በኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ( ዶ.ር) የሰንደቅ አላማ መስቀል ስነስርዓት የተከናወነ ሲሆን በስፍራው የተገኙ የሶስቱም ተቋማት ሠራተኞችና በአካባቢው ያሉ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በሀገሪቱ ብሔራዊ ሰንደቅ አላማ ስር አንድነትን በመጠበቅ ለሀገር እድገትና ብልጽግና የበኩላቸውን እንደሚወጡ በህብረት ቃል ገብተዋል፡፡