Uncategorized

መ/ቤቱ ለክልልና ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች የሚያደርገውን የአቅም ግንባታ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር /ፌዋኦ/ መ/ቤት ለክልልና ለከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች የሚያደርገውን የአቅም ግንባታ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ም/ ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ለክልልና ለከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች በቀጣይነት የአቅም ግንባታ ድጋፍ በሚደረግበት አግባብ ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡ ምክትል ዋና ኦዲተሯ ከክልልና ከከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር እና ምክትል ዋና ኦዲተሮች ጋር በነበራቸው ቆይታ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለክልልና ለከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች የስልጠና፣ ተሞክሮ የማጋራት እና የቁሳቁስ ድጋፎችን በተለያየ ጊዜ ሲያደርግ እንደነበረ አስታውሰው በቀጣይም መ/ቤቱ እነዚህን እና ሌሎች ድጋፎችን አቅም በፈቀደ መጠን እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

የክልልና የከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች የስራ ኃላፊዎችም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከዚህ ቀደም የተለያዩ የአቅም ግንባታ ድጋፎችን ሲያደርግ እንደቆየ አስታውሰው አሁንም ያሉባቸውን ችግሮችና ፍላጎቶቻቸውን በመጥቀስ መ/ቤቱ ቀጣይ እገዛ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡

በተለይም የሰው ሃይልን የማብቃትና የላፕቶፕ ኮምፒውተር ድጋፎችን በማድረግ ረገድ እያደረገ ያለው እገዛ የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸው አሁንም ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡

የመ/ቤቱ የትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አበራ ታደሰ በበኩላቸው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከክልልና ከከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች በቀረበለት የሥልጠና ፍላጎት እንዲሁም በመ/ቤቱ  የማሰልጠን አቅም መሠረት ቀጣይ የስልጠና ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው ይህ የሰው ኃይልን የማብቃት ድጋፍ ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *