ተቋማዊ አሠራሮች ስልጣን በተሰጠው ህጋዊ አካል በጸደቁ ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች መሰረት ሊተገበሩ እንደሚገባ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በትምህርት ምዘናዎችና ፈተናዎች አገልግሎት የ2013 በጀት ዓመት የሂሳብና ህጋዊነት ኦዲት አፈጻጸም ወቅት የታዩ የኦዲት ግኝቶችን መሠረት አድርጎ ባካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ላይ ተገለጸ፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተቋሙ ላይ ባካሄደው ኦዲት መሠረት በሚኒስትሮች ም/ቤት ሳይጸድቅና እንዲተገበር ሳይፈቀድ ለፈተናዎች ማስፈጸሚያ የሚሆን ከብር 1 ሚሊዮን በላይ ወጪ መደረጉ እና የክፍያ ተመን በሚመለከተው አካል ሳይጸድቅ ድጋሜ ለሚሰጡ የትምህርት ማስረጃዎች ከብር 13 ሺህ በላይ የአገልግሎት ክፍያ መሰብሰቡ በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡
ከዚህም ሌላ የመንግስት የግዥ መመሪያን የጣሰ የጥገና አገለግሎት ግዥ መፈጸሙ፣ ለበርካታ ዓመታት ሳይወራረድ የቆየ ከብር 56.3 ሚሊዮን በላይ ገንዘብ መገኘቱን ጨምሮ በበጀት ዓመቱ ለባለመብት መከፈል የነበረበትና ያልተከፈለ ከብር 16.2 ሚሊዮን በላይ ተካፋይ ሂሳብ መገኘቱ፣ በ2012 በተደረገ ኦዲት መሰረት ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ፈቃድ ሳይሰጥ ከህግና አሠራር ውጪ ለተወሰኑ የተቋሙ ሠራተኞች ለማጓጓዣ በሚል የተከፈለው ክፍያ ተመላሽ እንዲሆን የተሰጠው የኦዲት አስተያየት ያለመተግበሩ፣ እንዲሁም ሌሎች በርካታ የፋይናንስ እና የንብረት አስተዳደር ጉድለቶች መታየታቸውን ኦዲቱ እንደሚያሳይ ተገልጿል፡፡
የትምህርት ምዘናዎችና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ.ር እሸቱ ከበደን ጨምሮ በመድረኩ የተገኙ የአገለግሎት መ/ቤቱ አመራሮች የተጠቀሱት የኦዲት ግኝቶች ትክክለኛ መሆናቸውንና ህገ ወጥ የጥገና አገልግሎት ግዥ እንዲፈጸም ባደረጉ አካላት ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ጨምሮ አብዛኛዎቹን ግኝቶች ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በሚኒስትሮች ም/ቤት መጽደቅ የሚገባውና ለሀገር አቀፍ ፈተናዎች ፈተና ማስፈጸሚያ የሚውለው የፈታኞች የክፍያ ደንብ አስካሁን ድረስ ያልጸደቀ በመሆኑ ፈተናዎችን ማስቀረት በማይቻልበት ሁኔታ አገልግሎቱ ከፍተኛ የአሠራር ችግር ውስጥ መሆኑን የጠቀሱት አመራሮቹ ችግሩ ጊዜ የሚሰጥ ባለመሆኑ የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
አገልግሎቱ የኦዲት ግኝቶችን ለማስተካከል እያደረገ ያለው ጥረት የሚያበረታታ መሆኑንና ቀሪ ግኝቶችን በአስቸኳይ ማስተካከል የሚገባ መሆኑን በአስተያየታቸው የጠቀሱት የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው ህጎችን ፣ደንቦችንና መመሪያዎችን ስልጣን በተሰጣቸው ህጋዊ አካላት አጸድቆ አሠራርን መተግበር ይገባል ብለዋል፡፡
በተለይም ቀጣይ የፈተና ሂደቶች ላይ ችግር የሚፈጥር ከመሆኑ አንጻር ለሀገር አቀፍ ፈተናዎች ማስፈጸሚያ የሚሆነውን የክፍያ ደንብ በአስቸኳይ እንዲጸድቅ ማድረግ እንደሚገባ በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡
በ2013 በጀት ዓመት ከታዩ ግኝቶች መካከል የተወሰኑት ተስተካክለው መገኘታውን በ2014 በጀት ዓመት በተደረገው ኦዲት መረጋገጡን የጠቀሱት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በሰጡት አስተያየትም ከተቋሙ አቅም በላይ የሆኑት የሀገር አቀፍ ፈተናዎች ማስፈጸሚያ የክፍያ ደንብ እና ድጋሜ ለሚሰጡ የትምህርት ማስረጃዎች ከተገልጋዮች ለሚሰበሰበው የአገልግሎት ክፍያ የሚሆን ህጋዊ ተመን በሚመለከታቸው ህጋዊ አካላት በአፈጣኝ ጸድቀው በስራ ላይ እንዲውሉ አሳስበዋል፡፡
ከመንግስት ህግና መመሪያ ውጭ ለማጓጓዣ በሚል የተከፈለው ክፍያ ተመላሽ እንዲደረግ ጨምረው ያሳሰቡት ክብርት ዋና ኦዲተሯ ሌሎች የፋይናንስ አሠራርና የንብረት አስተዳደርን የሚመለከቱ ክፍተቶች በአፋጣኝ መታረም አለባቸው ብለዋል፡፡
የተሰጡ አስተያየቶችን መሰረት ያደረገ የተሻሻለ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ የድርጊት መርሀ ግብር በ10 ቀናት ውስጥ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብና አፈጻጸሙም በየ3 ወራት ሪፖርት እንዲደረግ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ አቅጣጫ ያስቀመጡት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስትያን ታደለ በበኩላቸው ተቋሙ የ76 ዓመታት የዳበረ ልምድ ያለው ሀገራዊ ጉዳይን የሚያስፈጽም ተቋም እንደመሆኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የአሠራር ግድፈቶቹን አስተካክሎ በህግና በሥርዓት መመራት አለበት ብለዋል፡፡