ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የፋይናንስና ኮሙኒኬሽን መ/ቤቶች ኦዲት ዳይሬክቶሬት ኦዲተሮች ከሀምሌ 25 -27/2014 ዓ.ም በተለያዩ የኦዲት አሠራሮች ላይ ያተኮረ የአቅም ማጎልበቻ የውስጥ ስልጠና በመ/ቤቱ የስልጠና ማዕከል ተሰጠ፡፡
ስልጠናው በሂሳብ ሪፖርት ፣ በኦዲት ሪፖርት፣ በግንባታ ሂሳብ ኦዲት እና በፋይናንሽያል ኦዲት የአሠራር ማኑዋል (FAM-Financial Audit Manual) የስልጠና ይዘቶች ላይ በማተኮር የተሰጠ ሲሆን ከሀምሌ 25-26 /2014 በነበሩት ሁለት ቀናት 44 ለሚሆኑ ኦዲተሮች በአጠቃላይ ይዘቶቹ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተካሂዷል፡፡
ከዚህም ሌላ ሀምሌ 27/2014 ዓ.ም የስልጠና ይዘቶቹን አተገባበር ወጥ በማድረግ ዙሪያ ከአጠቃላይ ሰልጣኞች የተውጣጡ 13 ከፍተኛ ኦዲተሮች እና 4 ስራአስኪያጆች የተሳተፉበት የአንድ ቀን የምክር ስልጠና ተካዷል፡፡
ስልጠናው በዋናነት በፋይናንስና ኮሙኒኬሽን መ/ቤቶች ኦዲት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በአቶ ጌታሁን ዳምጤ የተሰጠ ሲሆን የዳይሬክቶሬቱ ስራአስኪያጆች በአስተባበሪነት ተሳትፈዋል፡፡
በስልጠናው ማጠቃለያ ዳይሬክተሩ አቶ ጌታሁን ዳምጤ ስለ ስልጠናው ፋይዳ ተጠይቀው በሰጡት አስተያየት ስልጠናው የዳይሬክሬቱን የኦዲት አተገባበር በተመለከተ በዳይሬክቶሬቱ የሚገኙ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎችን ግንዛቤ ለማሳደግ እና በተለይም በተቋም ደረጃ በተካሄደው የኦዲተሮች ዝውውር ምክንያት ከሌሎች ዳይሬክቶሬቶች የስራ ክፍሉን የተቀላቀሉ ኦዲተሮች በዳይሬክቶሬቱ ከቆዩ ኦዲተሮች ጋር ወጥ የሆነ አሠራር እንዲኖራቸው ማስቻል ነው ብለዋል፡፡
መ/ቤቱ በተለያዩ ዘርፎች ለሚገኙ አመራሮችና ባለሙያዎች ተከታታይ የሆኑ ስልጠናዎችን በመስጠት የሠራተኞቹን አቅም በመገንባት ላይ የሚገኝ ሲሆን የዚህ ስልጠና ዋነኛ ዓላማም የዳይሬክቶሬቱን አመራሮችና ባለሙያዎች የፋይናንሽያል ኦዲት ሙያዊ ዕውቀት በበለጠ በማሳደግ ጥራት ያለው እና ውጤታማ የሆነ የኦዲት ተግባር መፈጸም መሆኑ ተገልጿል፡፡