በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተለያዩ የስራ መደቦች ላይ አዲስ ለተቀጠሩ ኦዲተሮች የተቋሙን ዓላማ፣ ተልዕኮ፣ አሠራርና ሌሎች ጉዳዮች በተመለከተ ከጥር 19 እስከ የካቲት 4/2017 ዓ.ም ለ12 ተከታታይ የሥራ ቀናት በመ/ቤቱ የስልጠና ማዕከል የመጀመሪያው ዙር የተቋማዊ ትውውቅ /Induction/ ስልጠና ተሰጠ፡፡
በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ የስልጠና ማስጀመሪያና መክፈቻ ንግግር በተጀመረው የመጀመሪያ ዙር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ማጠናቀቂያ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤና ም/ዋና ኦዲተሩ ክቡር አቶ አበራ ታደሠ የተገኙ ሲሆን ክብርት ዋና ኦዲተሯ በሰጡት የማጠቃለያ የስራ መመሪያ የኦዲት ስራ ልምድ እና በስነ-ምግባር የታነፀ ስብእና የሚያስፈልገው የስራ ዘርፍ መሆኑን ለሰልጣኖቹ ገልጸዋል፡፡
ሰልጣኞች ይህንን በመገንዘብ እራሳቸውን በዚህ ልክ ማዘጋጀት እንደሚገባቸው እና በሚሰማሩበት የስራ ቦታ ሁሉ የመ/ቤቱ አምባሳደር በመሆን ስራቸውን በመርህ ላይ የተመሰረተ እንዲያደርጉ ለሰልጣኞቹ ጨምረው ያሳሰቡት ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ከስልጠናው በኋላ የሚኖራቸው የስራ ጊዜ መልካም እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡
የመ/ቤቱ የኦዲት ዘርፍ ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ በበኩላቸው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በትምህርት የተገኘ እውቀት በተግባር የሚተረጎምበት ተቋም እንደሆነ አስረድተው ሰልጣኞች ወደ ስራ በሚገቡበት ወቅት የተቋሙን አሰራር በሚገባ ተረድተው በስልጠናው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር በሚመደቡበት የስራ መስክም ጥራቱን የጠበቀ ኦዲት በማከናወን ተአማኒነት ያለው ሪፖርት ማመንጨት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡
አያይዘውም አሁን የተሰጣቸው የትውውቅና ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሆኑን እና በቀጣይ ግን የሰራተኞች ክፍተት እየተለየ ለስራቸው የሚያግዛቸው የተለያዩ የአቅም ማጎልበቻ የስራ ላይ ስልጠናዎች እንደሚሰጡ ገልፀዋል፡፡
ሰልጣኞች በበኩላቸው በስልጠና ቆይታቸው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በአለም አቀፍ ስታንዳርድ የኦዲት ስራውን እንደሚያከናውን ግንዛቤ ያገኙ መሆኑን ጠቅሰው የመ/ቤቱን አሰራር ተከትለው ስራቸውን ማከናወን የሚያስችል ተገቢ እውቀት ከስልጠናው እንዳገኙ ገልፀዋል፡፡
በዚህ የመጀመሪያ ዙር የትውውቅ ስልጠና መርሀ ግብር በጥቅሉ 27 የሚሆኑ አዳዲስ የክዋኔ ኦዲተሮች የተሳተፉ ሲሆን የፋይናንሽያል ጀማሪ አዳዲስ ኦዲተሮችን ያሳተፈና ከየካቲት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለ12 ቀናት የሚቆይ ተመሳሳይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠት መጀመሩ ታውቋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በየጊዜው መ/ቤቱን ለሚቀላቀሉ አዳዲስ ሠራተኞች ከስራ በፊት የትውውቅና ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን በቋሚነት እያዘጋጀ እንደሚሰጥ ይታወቃል፡፡