News

ለመ/ቤቱ ባለሞያዎች በአስተሳሰብ ግንባታ (Mind set) እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ

ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የተለያዩ የስራ ክፍሎች ለተውጣጡ ባለሙያዎች በአስተሳሰብ ግንባታ /Mindset/፣ በአመራር ክህሎት /Leadership/፣ በስሜት ብልህነት /Emotional Intelligence/ እና በሌሎች ተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ ስልጠና ተሰጠ፡፡

ከየካቲት 13-25/2015 ዓ.ም በሁለት ዙሮች የተሰጠውን ስልጠና ከሰይድ እና እሱባለው የምክር፣ የማስታወቂያና የሥልጠና አገልግሎት ህብረት ሽርክና የመጡና በዘርፉ ላይ የዳበረ ልምድ ያላቸው የስልጠና ባለሙያዎች ሰጥተዋል፡፡

በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው ስልጠናውን የተመለከተ መልዕክት ያስተላለፉት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ ቀደም ሲል ለመ/ቤቱ የማኔጅመንት አባላት በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይ ላይ በእነዚሁ አሰልጣኞች የተሰጠውን ስልጠና በማስታወስ በስልጠናው የተገኘውን አቅምና መነሳሳት ወደ ተቋም በማውረድ ለተቋማዊ ተልዕኮ መሳካት ማዋል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

አክለውም ስልጠናው በግለሰብ ደረጃ ያለውን የህይወትና የስራ ስብዕና ከማዳበሩ ባሻገር ተቋማዊ ግቦችን በቡድናዊ የስራ ስሜት ለማሳካት ሊኖር የሚገባውን የእርስ በእርስ ግንኙነት ለማጠናከርም እገዛው የላቀ ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይም መሰል ስልጠናዎች ለሌሎችም የመ/ቤቱ ሰራተኞች የመስጠት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመልዕክታቸው የጠቀሱት ክቡር ም/ዋና ኦዲተሩ ቀደም ሲል ለማኔጅመንት አባላት የተሰጠውን ስልጠናም ሆነ ይህንን በሁለት ዙሮች ለ10 ቀናት የተሰጠውን ስልጠና በትብብርና ድጋፍ በሚባል ደረጃ ውጤታማና ማራኪ በሆነ መልኩ ለሰጠው የሰይድ እና እሱባለው የምክር፣ የማስታወቂያና የሥልጠና አገልግሎት ህብረት ሽርክና በእራሳቸውና በመ/ቤቱ ስም ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በስልጠናው የተሳተፉ የመ/ቤቱ አባላት በበኩላቸው ሥልጠናው በአስተሳሰብ ለውጥ ላይ በመመስረት የግል ህይወታቸውን በውጤታማ ደረጃ ለመምራትም ሆነ የሚጠበቅባቸውን መደበኛ ስራ ስኬታማ ለማድረግ የፈጠረባቸውን መነሳሳትና መነቃቃት ጠቅሰው በስልጠናው ያገኟቸውን ዕውቀትና ክህሎቶች ወደ ተግባር በመለወጥ ተጨባጭና ውጤታማ ስራዎችን እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

በአጠቃላይ በሁለቱ ዙሮች በተካሄደው ስልጠና 142 የሚሆኑ ሰልጣኞች መሳተፋቸው ታውቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *