News

ሁሉም የመንግስት ልማት ድርጅቶች በሂሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽን ኦዲት የማይሸፈኑ መሆኑ ተገለጸ

የሂሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽን ከመንግስት የልማት ድርጅቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ባካሄደው የምክክር መድረክ ሁሉም የመንግስት ልማት ድርጅቶች በኮርፖሬሽኑ ኦዲት የማይሸፈኑ እና ህጉ በሚያዘው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሂሳባቸውን ዘግተው ለኦዲት የማያቀርቡ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም በተካሄደው የምክክር መድረክ የተገኙት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ ባስተላለፉት መልዕክት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ለሀገር ልማትና እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱና የህዝብን የመልማት ፍላጎት ለማሳካት ዋነኛ አቅም እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

የልማት ድርጅቶች ለሀገር ልማትና እድገት አስተዋጽኦ ከማበርከት ባሻገር የመንግስት ሀብትና ንብረትን በተቀመጠው ህግና የአሠራር ሥርዓት መሠረት ሊያስተዳድሩ እንዲሁም የቁጥጥር ሥራዎችን ከሚሠሩ አካላት ጋር በትብብርና በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ ም/ዋና ኦዲተሩ አሳስበዋል፡፡

አያይዘውም በአሁኑ ወቅት በሂሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽን ኦዲት መደረግ ከሚገባቸው 34 ድርጅቶች መካከል 20ዎቹ ብቻ በኮርፖሬሽኑ ኦዲት እየተደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የመንግስት ልማት ድርጅቶች ህጉ በሚያዘው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሂሳባቸውን ዘግተው ለኦዲት ዝግጁ እንደማያደርጉ ያስታወሱት ክቡር አቶ አበራ በቀጣይ በኦዲት ሳይሸፈኑ የቆዩት 14 ድርጅቶችም በኮርፖሬሽኑ ኦዲት ሊደረጉ እና ሁሉም ድርጅቶች ሂሳባቸውን በወቅቱ ዘግተው ለኦዲት ዝግጁ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳሬክተር አቶ ደምሳሽ ጌታቸው በበኩላቸው የሂሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽን የመንግስት የልማት ድርጅቶች የተጠናከረ የፐብሊክ ፋይናንስ አስተዳደር አመራርና ቁጥጥር እንዲኖራቸው ለማስቻል የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አስታውሰው የዛሬው መድረክ የተዘጋጀው የጋራ ችግሮች ላይ በመምከር የመፈትሄ ሃሳብ ለማመንጨትና ውጤት ለማምጣት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ጋሼ የማነ እና ሌሎች የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች በበኩላቸው  የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እና የሂሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽንን የህግ መሠረቶች፣ ሥልጣንና ኃላፊነት፣ ኦዲቱ የሚከናወንበትን ሥርዓት እንዲሁም ኮርፖሬሽኑ በእቅዱ መሠረት  የደረሰበትን የኦዲት ሽፋን መጠንና ቀሪ ሥራዎች በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡

የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎችም በተነሱ ሀሳቦች እና በቀጣይ ሊሠሩ ይገባል ባሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ አስተያየትና ጥያቄዎችን አንስተው ከመድረኩ ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *