በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የህጻናት ማቆያ ማዕከል ቆይታ ያደረጉና ለቀጣዩ መደበኛ የመዋዕለ ህጻናት ትምህርታቸው ጠቃሚ የሆነ መሠረታዊ ዝግጅት ሲደረግላቸው የቆዩ የሁለተኛ ዙር ስድስት ህጻናት የማዕከል ቆይታቸውን አጠናቀዋል፡፡
በመ/ቤቱ የሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ጉዳይ ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት እየተመራ ያለውና የመ/ቤቱ ሠራተኞች ልጆች የሆኑ ህጻናትን በመቀበል እያስተናገደ ያለው ማዕከሉ ቀደም ሲልም ተመሳሳይ ቆይታ የነበራቸውን የአንደኛ ዙር ስድስት ህጻናት ለመሠረታዊ መደበኛ የመዋዕለ ህጻናት ትምህርት አዘጋጅቶና አብቅቶ ማውጣቱ ታውቋል፡፡
በህጻናቱ የማቆያ ማዕከል ቆይታ ማጠናቀቂያ መርሀ ግብር ላይ የተገኙት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ማዕከሉ ህጻናቱ በቆይታቸው በሞግዚቶቻቸው አማካይነት ለወደፊት የትምህርት እርከኖች መሠረታዊ የሚሆኑ ዝግጅቶችን የሚያደርጉበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል ማዕከሉን በአስፈላጊ ቁሳቁስና ግብአቶች የማደራጀት አበረታች ተግባር መከናወኑንና ወደፊትም መ/ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ ተጨማሪ ድጋፍ በማድረግ ይህን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ክብርት ዋና ኦዲተሯ ጨምረው ጠቅሰዋል፡፡
የህጻናት ማቆያ ማዕከሉ የመ/ቤቱ ባልደረባ የሆኑ እናቶች ልጆቻቸውን በማዕከሉ በማድረግና በቅርብ በመከታተል ያለ ሀሳብ መደበኛ ስራዎቻቸውን እንዲሰሩ በማድረግ በኩል ከፍተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑን የጠቀሱት ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ከዚህ ባሻገር ማዕከሉ ህጻናቱ በሚደረግላቸው እንክብካቤ በመልካም ስነ ምግባር የሚታነጹበትና ለቀጣይ ትምህርት እርከን የሚዘጋጁበት በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የህጻናት ማቆያ ማዕከል ከተመሰረተ ጀምሮ እድሚያቸው ለመደበኛ የመዋዕለ ህጻናት ትምህርት ያልደረሱ የመ/ቤቱን ሠራተኞች ህጻናት እየተቀበለ ሙያዊ ክህሎት ባላቸው ሞግዚቶች አማካይነት እንክብካቤ እያደረገ ይገኛል፡፡