የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አመራርና ሠራተኞች ከኦዲት አገልግሎት ኮርፖሬሽን ሠራተኞች ጋር በጋራ በመሆን “በመትከል ማንሠራራት” በሚል መሪ ቃል ሀምሌ 24 ቀን 2017 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ በ7ኛ አመት 700 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ተሳትፈዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ አራብሳ አካባቢ በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ችግኞች የተተከሉ ሲሆን የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ እና ሌሎች የመ/ቤቱ እና የኦዲት አገልግሎት ኮርፖሬሽን የበላይ አመራሮች እንዲሁም ሌሎች አመራሮችና ሠራተኞች በችግኝ ተከላው ላይ በመገኘት ተሳትፈዋል።
የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሩን ያስጀመሩት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ መ/ቤቱ በሀገሪቱ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ከተጀመረ አንስቶ ላለፉት ተከታታይ አመታት በመርሀ ግብሩ መሳተፉን ገልጸው ወደፊትም እንደሀገር የታቀደው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ የመትከል እንቅስቃሴ እስኪሳካ ድረስ ከኦዲቱ ስራ በተጓዳኝ የችግኝ መትከልና የመንከባከብ እንቅስቃሴው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሠራተኞች ላለፉት ተከታታይ አመታት በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ በሚገኙ አጎራባች አካባቢዎች በርካታ ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።