News

በመሠረታዊ ንግድ ክህሎትና ሥርዓተ ጾታ ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጠ

ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሴት ሠራተኞች በመሠረታዊ ንግድ ክህሎትና ሥርዓተ ጾታ ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጠ፡፡

ከጥር 6 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለ5 ቀናት የተሰጠው ስልጠና 40 የሚሆኑ የመ/ቤቱን ሴት ሠራተኞች ያሳተፈ ሲሆን ሴቶች መሠረታዊ የንግድ ክህሎትን አዳብረው በቁጠባና ብድር አገልግሎት በመጠቀም እንዴት ራሳቸውን ማገዝ እንደሚችሉ ዕውቀትንና ክህሎትን የሚያስጨብጥ መሆኑ ታውቋል፡፡

የስልጠና መድረኩ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ጉዳይ ዳይሬክቶሬት በኩል የተመቻቸ ሲሆን ስልጠናውን ከአዲስ አበባ ራስ አገዝ የሴቶች ድርጅት የመጡ የስልጠና ባለሙያ ሰጥተዋል፡፡

ሰልጣኞች በቆይታቸው ከመሠረታዊ ንግድ ክህሎት ባሻገር የስርዓተ ጾታን ጽንሰ ሀሳብ በሚመለከት ሰፊ ግንዛቤ የተሰጣቸው መሆኑም  ከሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ጉዳይ ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በስልጠናው ማጠቃለያ ስነስርዓት ላይ በመገኘት ለሠልጣኞች የተሳትፎ የምስክር ወረቀት የሰጡት የዋና ኦዲተር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አወቀ ጤናው ስልጠናውን አስመልክቶ ለሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት በስልጠናው ያገኛችሁትን ዕውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር በመቀየር በራሳችሁም ሆነ  በተቋሙ ላይ ለውጥ ማሳየት ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡

የስልጠናው ተሳታፊ ሠራተኞች በሰጡት አስተያየት ስልጠናው በአንድ ላይ በመደራጀት በብድር የመነሻ ካፒታል ማመንጨትን ጨምሮ  ከመደበኛ ስራ በተጓዳኝ እንዴት ራስ አገዝ በሆነ ሁኔታ የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ የግልንም ሆነ የቤተሰብ ህይወትን መለወጥ እንደሚቻል ጠቃሚ ግንዛቤ ያገኙበት መሆኑን ጠቅሰው ስርዓተ ጾታን በሚመለከት ያገኙት ሀሳብም ቀደም ሲል በዘርፉ ላይ ያላቸውን ዕውቀት ይበልጥ ያዳበረላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *