News

የአገልግሎት መ/ቤቱ የኦዲት ግኝቶችን የማስተካከል ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለጸ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ላይ በ2014 በጀት ዓመት እና ቀደም ባሉት ጊዚያት ባካሄዳቸው ኦዲቶች መሰረት የታዩ ግኝቶችን ለማስተካከል በአዲሱ የተቋሙ አመራር እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ተባለ፡፡

በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2014 በጀት ዓመት በተቋሙ ላይ የተካሄደውን የሂሳብ ኦዲት በተመለከተ የተቋሙ አመራሮች በተገኙበት ጥር 8 ቀን 2016 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ይፋዊ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሄዷል፡፡

በመድረኩ ተቋሙ ግኝቶችን ለማስተካከል ጥረት እያደረገ ቢሆንም ቀደም ሲል ከነበሩት ጊዜያት ጀምሮ ተንከባለው የመጡና አሁንም ድረስ ያልተፈቱ የፋይናንስና ንብረት አስተዳደር ክፍተቶች በርካታ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ከክፍተቶቹ መካከልም የመደበኛና የካፒታል ሂሳቦችን ሳይለዩ ቀላቅሎ የመመዝገብና የመጠቀም፣ ዝቅተኛ ዋጋ አቅራቢዎች እያሉ ከፍተኛ ዋጋ ያቀረቡ ድርጅቶች ግዥን እንዲያሸንፉ የማድረግ፣ በተለያዩ የባንክ ሂሳቦች መቀመጥ የሚገባቸው ሂሳቦች በአንድ የባንክ ሂሳብ እንዲቀመጡ የማድረግ፣ያለአግባብ የተከፈለ በመሆኑ ተመላሽ እንዲደረግ ቀደም ሲል በተካሄደ  ኦዲት አስተያየት የተሰጠበት  የውሎ አበል አስከአሁን ድረስ ተመላሽ እንዲሆን ያለማድረግ፣ በቂ የክፍያ ማስረጃ ሳይቀርብ ክፍያ የመፈጸም፣ በኮፒ ደረሰኝ ንብረትን ገቢ የማድረግ፣ ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳቦችን በወቅቱ ያለመፈጸምና ለረጅም ጊዜ የማቆየት እንዲሁም በጀትን በአግባቡ ያለመጠቀም እና ሌሎች ችግሮች በተደረገው ኦዲት መለየታቸው ተነስቷል፡፡

ከዚህም ሌላ በተሸከርካሪ አጠቃቀምና በግንባታ አፈጻጸም ያሉ ችግሮችን ጨምሮ በርካታ የንብረት አስተዳደር ክፍተቶች መኖራቸው በዝርዝር የተገለጸ ሲሆን በተነሱት የኦዲት ግኝቶች ላይ የተቋሙ አመራሮች ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠይቆ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌን (ዶ.ር) ጨምሮ የተቋሙ አመራሮች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በመድረኩ የተነሱት የኦዲት ግኝቶች ትክክለኛና አብዛኞቹም ቀደም ካሉት ጊዜያት ጀምሮ የመጡ መሆናቸውን  የገለጹት አመራሮቹ የክፍተቶቹ መነሻዎች በዋናነት የፋይናንስ አሠራር ችግር፣ የባለሙያ አቅም ማነስ፣ በዋና መ/ቤትና በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች መካከል ያለው ቅንጅታዊ አሠራር አነስተኛ መሆን እና የተቋማዊ አደረጃጀትና መዋቅር ችግር መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

አያይዘውም ተቋሙ ላለፉት ተደጋጋሚ አመታት ተቀባይነትን በሚያሳጣ የኦዲት አስተያየት ውስጥ የቆየ እንደመሆኑ የሠራተኞችን አቅም የማጎልበት ጥረቶችን ጨምሮ ችግሮቹን በዘለቄታ ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑንና በኣብዛኛዎቹ ግኝቶች ላይ ማስተካከያ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትና ባለድርሻ አካላት የተሰጡ ምላሽና ማብራሪያዎችን መሰረት በማድረግ በሰጡት አስተያየት የተቋሙ አዲስ አመራር የቆዩ ዘርፈ ብዙ የአሠራር ችግሮችን ለመቅረፍ እያደረገ ያለው ጥረትና እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት አበረታች ነው ብለዋል፡፡

አክለውም አገልግሎት መ/ቤቱ ቀደም ሲል በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ከባድ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው እንደመሆኑ ቀሪ ግኝቶችን ለማስተካከልና በተለይም በተከፋይና ተሰብሳቢ ሂሳቦች፣ በሂሳብ አመዘጋገብ፣ በግዥ ስርዓት፣ በበጀት አጠቃቀም እና በንብረት አስተዳደር ያሉ ክፍተቶች ሰፊና ከፍተኛ ትኩረት የሚሹ በመሆናቸው የማሻሻያ ጥረቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በተለይም መመሪያን በመጣስ ጥፋት በፈጸሙ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝና አስተማሪ መሆን እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክብር አቶ አበራ ታደሠ በሰጡት አስተያየትም ተቋሙ በላከው የኦዲት ግኝት ማሻሻያ የድርጊት መርሀ ግብር ላይ የተቀመጡ የማሻሻያ ሀሳቦች ወቅታቸውን ጠብቀው ተግባራዊ እንዲደረጉ፣ የአሠራር ዕቅድ ከስራ በፊት ቀድሞ እንዲዘጋጅና በአጥፊዎች ላይም ተመጣጣኝ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስበው ተስተካክለዋል የተባሉ ግኝቶች በቀጣይ የክትትል ኦዲት ይረጋገጣሉ ብለዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ላለፉት ሶስት ዓመታት በተደረጉ ኦዲቶች መሰረት ተቀባይነት በሚያሳጣ የኦዲት ግኝት አስተያየት ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ጠቁመው ተቋሙ ከቆየበት ውስብስብ ችግር አንጻር አዲሱ አመራር በርካታ ከሂሳብና ከንብረት ጋር የተያያዙ ችግሮችን የተረከበ እንደመሆኑ ብዙ ስራዎች ይጠብቁታል ብለዋል፡፡

በተለይም የመደበኛና የካፒታል በጀት ሂሳቦችን ለይቶ ያለመመዝገብ ክፍተት አሁንም ድረስ የቀጠለ መሆኑንና ያልተለመደና ህግን ያልተከተለ የካፒታል በጀትን ወደ መደበኛ በጀት አዙሮ የመጠቀም አሠራርን ጨምሮ ጉልህ የፋይናንስ ስርዓት ክፍተቶች በተቋሙ መኖራቸውን  ክብርት ዋና ኦዲተሯ ገለጸዋል፡፡

አያይዘውም የተለያዩ ሂሳቦችን አመዘጋገብ ባህሪ ያለመለየት ችግር ከአቅም ክፍተት ጋር የተያያዘ በመሆኑ የሠራተኞችን አቅም የማሳደግ ጥረት እንዲጠናክር እና በተለይም በግዥ ስርዓት፣ የግንባታዎችን ጨምሮ በፕሮጀክቶች ሂሳብ አሠራርና አፈጻጸም፣ በተሰብሳቢና ተከፋይ፣ በንብረት ገቢ ደረሰኞች ህጋዊነት እንዲሁም ሰፊ ክፍተት በሚታይበት የንብረት አስተዳደር እና ሌሎች አሠራሮች ላይ ተገቢ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ም/ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ ባነሱት የማጠቃለያ ሀሳብ የአገልግሎት መ/ቤቱ በነበሩበት የአሠራር ግድፈቶችና በታዩበት በርካታ የኦዲት ግኝቶች ሳቢያ ከቦታቸው የተነሱ ቀደም ሲል የነበሩ አመራሮቹን ጨምሮ ከባድ ማስጠንቀቂያና የገንዘብ ቅጣት የተጣለበት መሆኑን አስታውሰው የመ/ቤቱ ተልዕኮና ስራ ለሌሎች ተቋማት ሀገራዊ አሠራሮች መሰረታዊ መረጃዎች አመንጪ እንደመሆኑ ቀሪ ግኝቶችን እንዲያስተካክል አሳስበዋል፡፡

በተለይም አብዛኛዎቹ ችግሮች ከአቅም ማነስና በግዴለሽነት ከሚሰሩ ስራዎች የመነጩ በመሆናቸው በአዲሱ አመራር የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *