#የፌዴራል_ዋና_ኦዲተር መ/ቤት በ2014 በጀት ዓመት በቱሪዝም ሚኒስቴር ላይ ባካሄደው የሂሳብ ኦዲት መሰረት በርካታ የፋይናንስ፣ የግዥና የንብረት አስተዳደር አሠራር ችግሮች መታየታቸው ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው ታህሳስ 17 ቀን 2016 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት መድረክ ነው፡፡
በመድረኩ በተሰብሳቢና በገቢ ሂሳቦች አመዘጋገብ ላይ ክፍተት መታየቱ፣ በተተጋነነ ዋጋ የተፈጸመ የፕሮቶኮል አልባሳት ግዥ መከናወኑ፣ በአማካሪ ባለሙያ ሳይረጋገጥ የግንባታ ክፍያና የወጪ ትክክለኛነት የክፍያ ማስረጃ ያልቀረበበት ክፍያ መፈጸሙ ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ ባለፈም ክፍያዎች በወቅቱ ባለመከፈላቸው ተቋሙ ለተጨማሪ የቅጣት ክፍያ መዳረጉ፣ ህግን ባልተከተለ ሁኔታ ለኃላፊዎች መኖሪያ ቤት እድሳት ወጪ መደረጉ፣ ህግን ያልተከተለና ብክነት የታየበት የተሸከርካሪ ነዳጅ አጠቃም መታየቱ እና ሌሎች በርካታ የንብረት አስተዳደር፣ አያያዝና አጠቃቀም ስርዓት ጉድለቶች በኦዲቱ መታየታቸው በመድረኩ ተነስቷል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትር ክብርት አምባሳደር ናሲሴ ጫሊን ጨምሮ በመድረኩ የተገኙ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ሚኒስቴር መ/ቤቱ በ2014 ዓ.ም እንደገና ከመዋቀሩ በፊት ቱሪዝም ኢትዮጵያ በሚል በድጎማ የሚተዳደር ተቋም የነበረ መሆኑን ጠቅሰው በኦዲቱ የተገኙ የአሠራር ችግሮችም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እየተንከባለሉ የመጡ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ችግሮቹ ከሰው ኃይል የብቃት ማነስና ከአሠራር የመነጩ መሆናቸውንና ከኦዲቱ በኋላ በርካታ ማስተካከያዎች መደረጋቸውን ጠቁመው የሰው ኃይልን ለማብቃት ስልጠናዎች እየተካሄዱ መሆኑን እንዲሁም ቀሪ ችግሮችን ለመቅረፍም ጥረታቸው እንደሚቀጥልና ለዚህም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትንና የሌሎች አካላትን የተጠናከረ ድጋፍ እንደሚሹ ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙ የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው ሚኒስቴር መ/ቤቱ ግኝቶችን ለማስተካከል ያደረገው ጥረት አበረታች ቢሆንም በበርካታ ግኝቶች ላይ የታየው የአመራሩ ምላሽ የሚጠበቀውን ያህል ያለመሆኑን ገልጸው የአሠራር ክፍተት ባሳዩ አካላት ላይ ተጠያቂነት መረጋገጥ እንዳለበትና የውስጥ ኦዲትን በማጠናከር አሠራርን ማሻሻል እና ከህግ ውጪ የተከፈሉ ክፍያዎች ተመላሽ መደረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ በበኩላቸው ከምላሾቹ በኋላ በሰጡት አስተያየት የኦዲት ግኝት ማስተካከያ የድርጊት መርሀ ግብር ዘግይቶ መድረሱን ጠቅሰው በድርጊት መርሀ ግብሩ የተጠቀሱና ተጨማሪ ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች በዝርዝር በማንሳት በመርሀ ግብሩ ያልተጠቀሱ ግኝቶች መኖራቸውንም አንስተዋል፡፡
ማስተካከያ ተወስዶባቸዋል የተባሉት ግኝቶች በቀጣይ በሚደረግ የክትትል ኦዲት እንደሚረጋገጡ አክለው የጠቀሱት ክቡር ም/ዋና ኦዲተር አቶ አበራ ከህግ ውጪ ለኃላፊ መኖሪያ ቤት እድሳት በሚል የወጣውን ጨምሮ ህግና መመሪያን ያልተከተሉ የፋይናንስና የንብረት አስተዳደር ችግሮች ህጉን ተከትሎ እንዲስተካከሉ ጠይቀዋል፡፡
#የፌዴራል_ዋና-ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ #መሠረት_ዳምጤ በሰጡት አስተያየት ሚኒስቴር መ/ቤቱ በግኝቶች ላይ የወሰዳቸው ማስተካከያዎች አበረታች መሆናቸውን ጠቁመው ትክክለኝነታቸው በክትትል ኦዲት ይረጋገጣል ብለዋል፡፡
ዘግይቶ የተላከው የግኝት ማስተካከያ የድርጊት መርሀ ግብር ተገቢ በሆኑ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ተፈርሞ ያልተላከ መሆኑን ጨምረው የገለጹት ክብርት ዋና ኦዲተሯ ከህግና መመሪያ ውጪ ክፍያ በፈጸሙ አካላት ላይ የተወሰደ እርምጃ እንዲገለጽ ጠይቀዋል፡፡
አክለውም ለሚኒስቴር መ/ቤቱ የስራ ኃላፊዎች በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በኩል ለተሰጠው መኖሪያ ቤት እድሳት የወጣው ወጪ ህግን ያልተከተለ እንዲሁም በተከራይ አከራይ ውል መፈጸም የነበረበትና ከዕቅድ ውጪ የተደረገ መሆኑን በመጥቀስ ያለ አማካሪ ማረጋገጫ የተፈጸመውን ክፍያ ጨምሮ መንግስት ሊያገኝ የሚችለውን ገቢ ያሳጡ ያለውድድርና ከመመሪያ ውጪ የተፈጸሙ ግዥዎች ህገ ወጥ ናቸው ብለዋል፡፡
የግዥዎችን አማራጭ ለመጠቀም የሚመለከተውን የመንግስት አካል ፈቃድ ማግኘት እንደሚገባ በአስተያየታቸው የጠቀሱት ክብርት ወ/ሮ መሠረት በተጋነነ ዋጋ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ አቅም ያላገናዘቡ የፕሮቶኮል አልባሳት ግዥዎችና ወጥነት የሌለው የበላይ አመራሮች የቤት እድሳት እንዲሁም በውጭ ምንዛሬ የሚመጣን የሀገሪቱን ነዳጅ ለብክነትና ለብልሹ አሠራር የዳረጉ የተቋማት አሠራሮችን ለማስቀረት የገንዘብ ሚኒስቴር ወጥ የሆነ የአሠራር መመሪያ ማውጣት እንዳለበትና ንብረት ሳይመልሱ ከተቋሙ በለቀቁ አካላት የተወሰዱ የመንግስት ንብረቶች መመለስ አለባቸው ብለዋል፡፡
በሚኒስቴር መ/ቤቱ ላይ የጎሉ የፋይናንስ አሠራር ክፍተቶች መታየታቸውን በመግለጽ የማጠቃለያ አስተያየታቸውን የሰጡት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ በበኩላቸው በተቋማት አደረጃጀት ላይ የአመራር መለዋወጥ ቢኖርም ተቋማት ቋሚ በሆነ የአሠራር ስርዓት መመራት እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም በግዴለሽነትና በተጋነነ ዋጋ የተፈጸመው የፕሮቶኮል አልባሳት ግዥ እና ለኃላፊ መኖሪያ ቤት እድሳት የወጡት ወጪዎችን ጨምሮ ህግን ላልተከተሉ የፋይናንስ አሠራር ግድፈቶች ምክንያት በሆነው የሚኒስቴር መ/ቤቱ የፋይናንስ ክፍል ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ እንዲሁም ከህግ ውጪ ለቤት እድሳት የወጣው ወጪ እንዲመለስ እና በመድረኩ የተሰጡ አስተያየቶችን መሰረት ያደረገ የድርጊት መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ አስከ ታህሳስ 25 ቀን 2016 እንዲቀርብ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡