News

የኮሚሽኑ የፋይናንስና ንብረት አስተዳደር አሠራር ጉልህ ክፍተቶች አሉበት ተባለ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2014 በጀት ዓመት በአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ላይ ባካሄደው የሂሳብ ኦዲት መሰረት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ አካሂዷል።

በ 2014 በጀት አመት በተካሄደው ኦዲት መሰረት በኮሚሽኑ ሰነዶቻቸው የጠፉ፣ ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ የተመዘገቡ እና በኮፒ ሰነዶች የተፈጸሙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ክፍያዎች መኖራቸው፣ ህግን ባልተከተለ አግባብ የሠራተኞች የዓመት ፈቃድ በገንዘብ ተቀይሮ መከፈሉ እና ህጋዊ ቅጽ ሳይሞላ አበል መከፈሉ እንዲሁም የበጀት አጠቃቀም ክፍተት መታየቱን ጨምሮ ጉልህ የፋይናንስና ንብረት አስተዳደር ስርዓት ክፍተቶች መታየታቸው በመድረኩ ተገልጿል።

በመድረኩ የተነሱ የግኝት ጥያቄዎች የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር አቶ ነሲቡ ያሲንን ጨምሮ በመድረኩ በተገኙ የተቋሙ አመራሮች ምላሽ የተሰጠባቸው ሲሆን የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ግኝቶቹንና ከተቋሙ አመራሮች የተሰጡ ምላሾችንና ማብራሪያዎችን አስመልክቶ አስተያየቶችን ተሰጥተዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሠ ከኮሚሽኑ አመራሮች ምላሽ በኋላ በሰጡት አስተያየት በግኝቶቹ ላይ ተወሰዱ የተባሉት ማስተካከያዎች በክትትል ኦዲት የሚረጋገጡ መሆኑንና በአጥፊዎች ላይ መካሄድ የሚገባውን የተጠያቂነት እርምጃ ጨምሮ በድርጊት መርሀ ግብሩ በተቀመጠላቸው ጊዜ ያልተተገበሩ የማስተካከያ እርምጃዎች መኖራቸው ተገቢ ያለመሆኑን አንስተው ሌሎች የተሟላ ምላሽ ባልተሰጠባቸው ግኝቶች ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ቀደም ሲል በነበሩ ዓመታትም ተጠያቂነትን ያስከተሉ ችግሮች የታዩበትና በቅርቡ በ2013 በጀት ዓመት በተደረገ ኦዲት የታዩ ግኝቶች ሳይስተካከሉ በ2014 በጀት ዓመት መታየታቸውን ጠቅሰው በተቋማዊ መዋቅር ላይ ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰብ ላይ ሊተገበር የሚገባ መሠረታዊ ሪፎርም ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡

የኦዲት ግኝቶቹን በዝርዝር ያነሱት ክብርት ዋና ኦዲተሯ አበልን ጨምሮ ያለአግባብ የተከፈለ የመንግስት ገንዘብ እንዲመለስ እና ጠፉ በተባሉት የክፍያ ሰነዶች ላይ ጥልቅ ፍተሻ እንዲደረግ አሳስበው ከህዝብ በተሰበሰበ ግብር እንዲሁም በእርዳታና በብድር ተገዝተው የሚመጡ የሀገሪቱ ንብረቶች አያያዝና አጠቃቀም ትኩረት እንዲሰጠውና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም ተቋሙን በማገዝ ረገድ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ በሰጡት አስተያየት ከድርጊት መርሀ ግብር ዝግጅት ባሻገር መርሀ ግብሩን ወደ ተግባር በመለወጥና በአጥፊዎች ላይ ተጠያቂነትን በማስፈን ረገድ ተገቢ ስራ ያልተሰራ መሆኑን ጠቅሰው አስከ ታህሳስ 10 ቀን 2016 የተሰጡ አስተያየቶችን መሰረት ያደረገ የድርጊት መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ እንዲሁም ያለ ህጋዊ ሰነድ እና ከህግ ውጪ የተከፈሉ ክፍያዎች እንዲመለሱ እና የዚህና የሌሎች ግኝቶች የማሻሻያ እርምጃዎች አፈጻጸም በሪፖርት እንዲቀርብ አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *