News

የዩኒቨርሲቲው የአካባቢ ምርምር ትግበራ ክፍተቶች እንዲስተካከሉ ተጠየቀ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ምርምር ስራዎች እና ለምርምሩ በሚውሉ ፈንዶች አጠቃቀም ላይ በ2014/2015 ኦዲት ዓመት ባካሄደው የክዋኔ ኦዲት የታዩ ግኝቶች መስተካከል እንዳለባቸው ህዳር 26 ቀን 2016 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በተካሄደው ይፋዊ የውይይት መድረክ ተጠየቀ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የምርምር ጭብጦች ወቅታዊነት፣ በምርምር ውጤቶች ችግር ፈቺነት፣ ተደራሽነትና ተግባራዊነት፣ የአካባቢ ብክለትን በመከላከልና በቆሻሻ አወጋገድ እንዲሁም በተመራማሪዎች የምርምር ስራ ቁጥጥር እንዲሁም ስነ ምግባር እና ተጠያቂነት፣ በምርምር ፈንዶችና ሀብት እንዲሁም ግብአቶች አጠቃቀምና አያያዝ እንዲሁም በሌሎች ተዛማጅ የምርምር ሂደቶች ዙሪያ ጥቂት የማይባሉ ከፍተቶች በኦዲቱ ወቅት መታየታቸው በመድረኩ ተነስቷል፡፡

የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጀማል የሱፍ (ዶ.ር) ጨምሮ በመድረኩ የተገኙ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ከኦዲቱ በኋላ የተጠቀሱትን ግኝቶች ለማስተካከል ስራዎች መሰራታቸውንና ቀሪ ስራዎችም እየተከናወኑ መሆኑን ባቀረቡት ዝርዝር ማብራሪያ ጠቅሰው የአካባቢ የምርምር ስራዎችን የበለጠ ውጤታማ፣ ለህብረተሰቡና ለሀገር ተግባራዊ ለውጥ የሚያመጡና ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ለማድረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየሠሩ መሆኑን ጠቁመው በተለይ የተለያዩ ግብአቶችን በማግኘት ሂደት ያለው የግዥ ስርዓት ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሠ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ምላሽ በኋላ በሰጡት አስተያየት ምርምሮች ከተቀመጠላቸው ጊዜ በላይ የሚዘገዩና የሚጓተቱ መሆኑን የኦዲቱ ግኝት የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመው ከላይ የተጠቀሱና ሌሎች በዩኒቨርሲቲው አመራሮች ተገቢ ምላሽ ያልተሰጠባቸውን ጉዳዮች በዝርዝር በማስቀመጥ ለግኝቶቹ ተገቢ ማስተካከያ እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙ የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው አንጋፋና ትልቅ የምርምር ተቋም እንደመሆኑ ከምርምር ስራ ጋር በተያያዘ የታዩትን ግኝቶች ማስተካከልና የበለጠ ሀገራዊ ጠቀሜታ ያለው ስራ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ኦዲቱ በምርምር ስራዎች እና አስተዳደር ቀልጣፋነትና ውጤታማነት እንዲሁም በምርምር ውጤቶች ተደራሽነትና ቅንጅታዊ አሠራር ላይ ትኩረቱን አድርጎ የተካሄደ መሆኑን አስታውሰው ምርምሮች በተከታታይ ሁኔታ ወቅታዊውን ሁኔታ ታሳቢ አድርገው እንዲሁም ለአካባቢ ጉዳትና የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ትኩረት ሰጥተው መካሄድ አለባቸው ብለዋል፡፡

አክለውም የምርምር ስራዎች የሀገር በቀል ዕውቀትን ከሳይንሳዊ ምርምሮች ጋር በማቀናጀት ለባህላዊ መድሃኒቶች የሚውሉ ዕጽዋት ለህብረተሰቡ ጠቀሜታ በሚሰጡበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ማድረግ የሚገባቸው መሆኑንና የምርምር ውጤቶች መረጃዎችንም በአግባቡ መያዝ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

አንድ የምርምር ስራ ከተጠናቀቀና ከተተገበረ በኋላ የውጤታማነት ግምገማ እንደሚያስፈልግ ጨምረው የገለጹት ክብርት ዋና ኦዲተሯ የምርምር ውጤቶችን በወቅቱ የማያስረክቡ ተመራማሪዎችም መጠየቅ እንደሚገባቸውና በቤተ ሙከራ አደረጃጀትና መሳሪያዎች አጠቃቀም ላይ ተገቢ ትኩረት መስጠትና በስራ ላይ ያልዋሉ ትርፍ መሳሪያዎች ካሉ ለሌሎች የቤተ ሙከራ ግብአትና መሳሪያ እጥረት ላለባቸው የትምህርትና ምርምር ተቋማት መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡

የሀሮማያ ሀይቅን ተፈጥሮአዊ ሁኔታ መጠበቅና መንከባከብ እንደሚገባ በአስተያየታቸው መጨረሻ የጠቀሱት ክብርት ወ/ሮ መሠረት በአካባቢው የሚካሄዱ የውሀ ጉድጓድ ቁፋሮዎች፣ የሀይቁን ውሃ በመጠቀም የሚተገበሩ የመስኖ ስራዎችና የፍሳሽ ቆሻሻዎችን ወደ ሀይቁ የማስገባት አዝማሚያዎች የሀይቁን ተፍጥሮአዊ ሁኔታ የሚያዛቡና መጠኑንም በመቀነስ ረገድ ቀደም ሲል የተከሰተውን የሀይቁን ድርቀት የሚያስከትሉ በመሆናቸው ለአካባቢው ህብረተሰብ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ መሰራት አለበት ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምር ስራ በሚሊዮን የሚቆጠሩ በርካታ ገንዘቦችን የሚጠቀም መሆኑንና በዚህ የገንዘብ ወጪ አመዘጋገብ እና አጠቃቀም ረገድ በኦዲቱ የታዩ ክፍተቶች መስተካከል የሚኖርባቸውና ወጪዎቹም ውጤት ማስገኘት ያለባቸው መሆኑን በመጥቀስ የማጠቃለያ አስተያየታቸውን የሰጡት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ ዩኒቨርሲቲው የተጠቀሱትን የኦዲት ግኝቶች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እንዲያስተካክልና ለዚህም የተሻሻለ የድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅቶ አስከ ታህሳስ 10 ቀን 2016 ዓ.ም እንዲያቀርብ እንዲሁም እስከ ጥር 15 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ የፈንድ አስተዳደር መመሪያውን አፅድቆ በተግባር እንዲያውል አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *