የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2014/2015 ኦዲት ዓመት በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ መረጃ አስተዳደር ሥርዓት ላይ ባካሄደው የክዋኔ ኦዲት የታዩ ግኝቶችን አስመልክቶ በተካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት መድረክ የሀገሪቱ የታክስ መረጃ አስተዳደር ሥርዓት ጊዜው በሚጠይቀው ቴክኖሎጂ ታግዞ የበለጠ መጠናከር ይገባዋል ተባለ፡፡
የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከኦዲት ባለድርሻ አካላትና ከገቢዎች ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ጋር ህዳር 21 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው መድረክ እንደተገለጸው በኦዲቱ ወቅት የታክስ መረጃ አስተዳደር ሥርዓትን የሚመለከቱ በርካታ ክፍተቶች ታይተዋል፡፡
አዋጅ ማስፈጸሚያ ረቂቅ መመሪያ ባለመጽደቁ በግብር አሰባሰብ ላይ የአሠራር ክፍተት መፈጠሩ፣ የታክስ እዳንና የግዥና የሽያጭ መረጃዎችን ጨምሮ በቂ የታክስ መረጃ አመዘጋገብ፣ አሰባሰብ፣ አደረጃጀትና፣ ትንተና ያለመደረጉ እንዲሁም ዘመኑ በሚጠይቀው ወቅታዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ በቂ የመረጃ አስተዳደር ሥርዓት ያለመኖሩ በኦዲቱ ወቅት መታየቱ በመድረኩ ላይ ተጠቅሷል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ለግብር ከፋዮች መረጃን ተደራሽ ከማድረግና ሀብትና ንብረታቸውን ከመመዝገብ እንዲሁም በግብር ከፋዮች እጅ የሚገኙ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያዎች (Cash Register Machines) ወቅቱን ከሚመጥኑ ቴክኖሎጂዎች ጋር ያልተሳለጡ እና ከግብር ከፋዮች የሚፈለጉ ተከታታይና ወቅታዊ መረጃዎችን በሚፈለገው ደረጃ ወደ መረጃ ቋት በማስገባት ሂደት ችግር ያለባቸው መሆኑ እንዲሁም የታክስ ማጭበርበርን ለመከላከል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቂ የሆነ ቅንጅታዊ አሠራር ያለመኖሩ ተጠቁሟል፡፡
የቀረቡትን የኦዲት ግኝቶች አስመልክቶ የገቢዎች ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ አይናለም ንጉሴና ሌሎች የሚኒስቴር መ/ቤቱ አመራሮች ሰፊ ምላሾችንና ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል፡፡
በተሰጡ የኦዲት ማስተካከያ አስተያየቶች መሰረት በኦዲቱ ወቅት የታዩት ግኝቶችን ለማስተካከልና በተለይም የታክስ መረጃ አስተዳደር ሥርዓቱን ጊዜው በሚፈቅደው ቴክኖሎጂ እንዲመራ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት የሚኒስቴር መ/ቤቱ አመራሮች በተለይም ቀደም ሲል በስራ ላይ የዋሉት የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያዎች ከግብር ከፋዮች ጋር የተያያዙ አስፈላጊ መረጃዎችን በሚፈለገው ደረጃ አደራጅቶ በማስተላለፍ ረገድ የነበረባቸውን ክፍተት ሊሞላ የሚችል ቴክኖሎጂ ለማበልጸግ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ቅንጅታዊ ስራ እየተሰራ መሆኑንና ጠቁመዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው በ2006 ዓ.ም በተመሳሳይ ሁኔታ በተቋሙ ላይ በተካሄደው ኦዲት የታዩ ክፍተቶች ሳይሻሻሉ በአሁኑ አዲትም መታየታቸውን አስታውሰው ከኦዲት ሪፖርቱ በኋላ በርካታ የማሻሻያ እርምጃዎች እንደተወሰዱ የተገለፀውን በክትትል ኦዲት የሚረጋገጥ መሆኑን ገልጸዋል።
የመረጃ መስጫ ማዕከላትን ከማጠናከር፣ ከሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያዎች ምዝገባና ጥገና፣ ጊዜው በሚፈቅደው ቴክኖሎጂ በመታገዝ የታክስ መረጃ አስተዳደር ሥርዓቱን የበለጠ ውጤታማና አስፈላጊ የግብር ከፋይ መረጃዎችን በተሻለ ቴክኖሎጂ መዝግበው እንዲያስተላልፉ ከማድረግ፣ ግብር ከፋዮችን ጨምሮ ተገቢ ከሆኑ ባለድርሻዎች ጋር ሊኖር የሚገባውን ቅንጅታዊ አሠራር ከማጠናከር አንጻር ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በሌላ በኩል ዋና ኦዲተሯ የገቢ መሰብሰቢያ ስርዓቶቻቸው የኦዲት መከታተያ መተግበሪያ ሊኖራቸው፣ የሚያለሟቸው ስርዓቶች እርስ በርስ ሊመጋገቡ እና መረጃ በአግባቡ ተደራሽ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበው ይህን በቀጣይ ተግባራዊ የሚያደርጉ ከሆነ ኢኮኖሚውን መሸፈን የሚችል ገቢ መሰብሰብ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ከኦዲቱ በኋላ የተሰጡትን የኦዲት ግኝት ማሻሻያ አስተያየቶች መሰረት በማድረግ የተወሰዱ እርምጃዎች አበረታች መሆናቸውን የገለጹት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ በበኩላቸው ከኦዲቱ በኋላ ተሰርተዋል ተብለው በሚኒስቴር መ/ቤቱ አመራሮች የቀረቡ ተግባራት በቀጣይ የክትትል ኦዲት የሚረጋገጡ ናቸው ብለዋል።
ሀገሪቱን ከእርዳታ ተላቃ ራሷን እንድትችል ለማድረግ እና ገቢዋንም ለመጨመር የታክስ ስርዓቱን በተለይም የታክስ መረጃ አሰባሰብ ሥርዓቱን በአሠራርና ወቅቱን በሚመጥን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ግብአት ማጠናከር እና የታክስ ማጭበርበርን ለማስቀረትም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሠራር የበለጠ ማሳደግ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡