በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የዘንድሮው የአለም አቀፍ የኤድስ ቀን እና የፀረ-ጾታዊ ጥቃት መገለጫ የሆነው የነጭ ሪቫን ቀን ተከበረ፡፡
ህዳር 18 ቀን 2016 ዓ.ም በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተካሄደው የአከባበር ስነስርዓት ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤን ጨምሮ የመ/ቤቱ አመራሮችና ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡
በስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ የነጭ ሪቫን ቀን አከባበር መነሻንና የጾታዊ ጥቃት ምንነትን እንዲሁም የኤች. አይ.ቪ ኤድስን በተመለከተ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡
የጾታዊ ጥቃትም ሆነ የኤች. አይ.ቪ ኤድስ በተቋም ደረጃ ካላቸው አሉታዊ ተጽዕኖ ባሻገር በሀገርም ሆነ በህብረተሰብ ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ተገንዝቦ ሁሉም የመ/ቤቱ ሠራተኛ በመከላከሉ ሂደት የየራሱን ድርሻ እንዲወጣ በንግግራቸው ላይ ያሳሰቡት ክብርት ዋና ኦዲተሯ በተለይም የመ/ቤቱ ኦዲተሮች አብዛኛውን የስራ ጊዜቸውን ከቦታ ቦታ በመዘዋወር በመስክ ስራ የሚያሳልፉ በመሆናቸውና ለእነዚህ ጉዳቶች የመጋለጥ ዕድላቸውም የሰፋ በመሆኑ ራስን በመጠበቅ ሂደት ልዩ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ብለዋል፡፡
የዘንድሮው የነጭ ሪቫን ቀን “Invest to Prevent Violence Against Women & Girls” በሚል መሪ ቃል በአለም አቀፍ ደረጃ ለ32ኛ ጊዜ እና “መችም፣ የትም፣ በምንም ሁኔታ ጾታዊ ጥቃትን ዝም አንበል” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ ጊዜ እንዲሁም የዘንድሮው አለም አቀፍ የኤድስ ቀን “የማህበረሰብ መሪ ለላቀ ኤች.አይ.ቪ መከላከል” በሚል መሪ ቃል ለ37ኛ ጊዜ በአለም አቀፍ ደረጃ እየተከበረ መሆኑ በስነስርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኤች.አይ.ቪ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ታመነ ጌታሁን አለም አቀፍ የኤድስ ቀንንና የኤች አይ ቪ ኤድስን ምንነት፣ ስርጭት እንዲሁም የመከላከል እርምጃዎችን አስመልክቶ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን በመቀጠልም የሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ኃይለስላሴ ንጉስ የነጭ ሪቫንን ምንነትና የጾታዊ ጥቃት መገለጫዎችን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በመጨረሻም የቀረቡትን ገለጻዎች መሰረት በማድረግ በስነስርዓቱ ተሳታፊዎች የጥያቄና መልስ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡