የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በአለም አቀፍ የኦዲት ስታንዳርዶች መሠረት እያከናወናቸው ስላሉ ኦዲቶች እና የመንግስት ኦዲት( Public Audit) ምንነት እንዲሁም የምክር ቤት አባላት በኦዲት አሠራር ላይ ስላላቸው ጉልህ ሚና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ፡፡
ከህዳር 8-9/2019 ዓ. ም በአዳማ ከተማ በተካሄደው የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀ ግብር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የተሳተፉ ሲሆን የአለም አቀፍ የኦዲት ስራ እና የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አመሰራረት፣ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴን ጨምሮ በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ቋሚ ኮሚቴዎች (Public Account Committees-PAC) በኦዲት አሠራር ላይ ስላላቸው ወሳኝ ሚና እንዲሁም የመንግስት ኦዲት (Public Audit) አጠቃላይ ምንነት በስልጠናው ተዳሷል፡፡
በቀረቡት የስልጠና ርዕሶች ላይ ሰፊና ዝርዝር ገለጻ የቀረበ ሲሆን ከገለጻው በኋላ በመድረኩ ተሳታፊዎች ጥያቄዎችንና ምላሾችን መሰረት ያደረገ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በስልጠናው ላይ እንደተገለጸው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እየሠራ ያለው የኦዲት ስራ የሜክሲኮና የሊማ ዴክላሬሽኖች ላይ የተቀመጡትን ጨምሮ ወቅታዊ የሆኑ የአለም አቀፍ የኦዲት ስታንዳርዶችንና የአለም አቀፍ ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ማህበር (INTOSAI) እንዲሁም የአፍሪካ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ሀገራት የዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ማህበር(AFROSAI-E) የኦዲት አሠራሮችን መሠረት ያደረገ መሆኑ ተብራርቷል፡፡
ከዚህም ሌላ የመ/ቤቱን የኦዲት ስራ ከሚቆጣጠረውና በየጊዜው የሚቀርቡለትን የኦዲት ሪፖርቶች መሰረት አድርጎ በግኝቶች ላይ በህዝባዊ ይፋዊ መድረኮች ከባለድርሻ አካላትና ከኦዲት ተደራጊ ተቋማት ጋር በጋራ በሚካሄዱ መድረኮች መሰረት ደረጃቸውን የጠበቁ የተለያዩ እርምጃዎችን የመውሰድ ግንባር ቀደም ኃላፊነት ካለበት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር ያለውን የስራ ግንኙነት በሚመለከት ዝርዝር ገለጻ ቀርቧል፡፡
የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ የግንዛቤ ማስጨበጫው የመ/ቤቱን የኦዲት ስራ በተመለከተ ሰፊ ሀሳብ የተነሳበት መሆኑንና በአለም አቀፍ ደረጃ ስላሉት የኦዲት አሠራሮችም መሰረታዊ ዕውቀት የተገኘበት መሆኑን ጠቅሰው ሊብራሩ በሚገባቸው ነጥቦች ላይ ጥያቂዎች አቅርበዋል፡፡
የቀረቡትን የማብራሪያ ጥያቄዎች መሰረት አድርጎም የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ ምክትል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሠ እና ሌሎች የመ/ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ሰፊ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በመድረኩ ማጠቃለያ ሀሳባቸውን የሰጡት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ የቀረበው ስልጠና ቋሚ ኮሚቴው የመ/ቤቱንም ሆነ የአለም አቀፉን የኦዲት አሠራር በጥልቀት እንዲረዳ ያደረገና መ/ቤቱን በበለጠ ለመደገፍ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ያመላከተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡