በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የኦዲት_ባለድርሻ_አካላት የትብብር ፎረም የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም ውጤታማ እንደነበር ተገለጸ፡፡
ህዳር 5 ቀን 2016 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በተካሄደው የፎረሙ መድረክ እንደተገለጸው የፌዴራል_ዋና_ኦዲተር መ/ቤት ባቀረባቸው የኦዲት ሪፖርቶች መሰረት በፎረሙ የጋራ ቅንጅት በ2015 በጀት ዓመት የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ እና ለ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ መሳካት መሰረት የጣሉ ናቸው ተብሏል፡፡
በመድረኩ ላይ የቀረበው ዝርዝር የአፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያሳየው የ2015 በጀት ዓመት የፎረሙ ዕቅድ በዝግጅት እና በትግበራ ምዕራፎች ተከፋፍሎ የተፈጸመ ነው፡፡
በፎረሙ የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ የዝግጅት ምዕራፍ የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ ግምገማና የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት መደረጉ የተገለጸ ሲሆን በዚሁ ምዕራፍ ለባለድርሻ አካላቱ የዕቅድ አፈጻጸም የስራ መመሪያ ተዘጋጅቷል ተብሏል፡፡
በፎረሙ የትግበራ ምዕራፍ በበጀት ዓመቱ በተለያዩ ሁኔታዎች ላይ ከተካሄዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀ ግብሮች ባሻገር የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2014 መጨረሻ ላይ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያቀረበውን የ2013 በጀት የኦዲት ሪፖርት መሰረት በማድረግ ከኦዲት ተደራጊ ተቋማት ጋር የተካሄዱ 28 ይፋዊ ህዝባዊ ውይይቶችና 5 የገጠር እና 3 የከተማ በድምሩ 8 የመስክ ምልከታዎች መደረጋቸው በቀረበው ሪፖርት ላይ ተገልጿል፡፡
በተካሄዱት ይፋዊ ህዝባዊ ውይይቶችና የመስክ ምልከታዎች ላይ በፎረሙ አባላት በተሰጡ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ አስተያየቶች መሰረት የኦዲት ተደራጊ ተቋማቱን የኦዲት ግኝቶች ያስተካከሉ ፍሬያማ ውጤቶች መመዝገባቸውን ሪፖርቱ አብራርቷል፡፡
በተሰጣቸው የኦዲት ግኝት አስተያየቶች መሰረት የማስተካከያ እርምጃ ባልወሰዱና ተጨባጭ የሆኑ ብልሹ አሠራሮችን ባሳዩ የተቋማት አመራሮች ላይ ከማስጠንቀቂያ እስከ ገንዘብ ቅጣት ድረስ ህግን የተከተሉ እርምጃዎች መወሰዳቸው በሪፖርቱ የተመለከተ ሲሆን በበጀት ዓመቱ ይፋዊ ውይይትና የመስክ ምልከታ የተደረገባቸው የፋይናንሽያል እና የክዋኔ ኦዲት በርካታ ግኝቶች ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተናጠልና የፎረሙ አባላት በጋራ በሰጧቸው የማስተካከያ አስተያየቶችና ባደረጓቸው ክትትሎች መሰረት በርካታ ገንዘብና ንብረቶች ለመንግስት ገቢ መደረጋቸው በአኃዝ ተጠቅሶ በዝርዝር ተገልጿል፡፡
በፎረሙ የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ላይ አበረታች የሆኑ በርካታ ጠንካራ ጎኖች መኖራቸው የተጠቀሰ ሲሆን በአንጻሩ በመስክ ጉብኝት አፈጻጸም፣ በአቅም ግንባታ ሥልጠና፣ በይፋዊ ውይይት እና በመስክ ምልከታ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እና ኦዲት ተደራጊዎች ለኦዲት ግኝት አስተያቶች ባላቸው ቁርጠኛ ምላሾች ዙሪያ የታዩ ክፍተቶች ተነስተዋል፡፡
የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸሙን በመነሻነትና የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ግኝቶችን መሰረት ያደረገ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎችን በቁልፍ ተግባርነት የያዘው የ2016 በጀት ዓመት የፎረሙ ዕቅድ ከአፈጻጸም ሪፖርቱ በኋላ በዝርዝር ቀርቧል፡፡
በበጀት ዓመቱ በፋይናንሽያልና በክዋኔ ኦዲት ግኝቶች ላይ በሚደረጉ በጥቅሉ 31 ይፋዊ ህዝባዊ ውይይቶችና በገጠርና በከተማ በሚደረጉ 19 የመስክ ምልከታዎች በሚሰጡ የማስተካከያ አስተያየቶችና በሚከናወኑ የክትትልና ድጋፍ ስራዎች መሰረት የኦዲት ግኝቶችን በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ መታቀዱን በቀረበው የፎረሙ የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ተጠቅሷል፡፡
የትብብር ፎረሙ ተሳታፊ አካላት በቀረበው የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ በዝርዝር የተወያዩ ሲሆን የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት_ዳምጤ የቀረበውን የአፈጻጸም ሪፖርት እና ዕቅድ መሰረት አድርገው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የ2015 በጀት ዓመት የፎረሙ አፈጻጸም በዕቅዶቹ የተቀመጡትን ተግባራት ያመላከተና የሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረት የታየበት መሆኑን በአስተያየታቸው መነሻ የጠቀሱት ክብርት ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሰረት በመድረኩ የቀረበው የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድም ቀደም ካሉት ጊዜያት ከነበሩት ዕቅዶች ሰፊና ባለድርሻ አካላቱን ሊያሳትፍ የሚችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በዕቅድ በተያዙት ይፋዊ ህዝባዊ የውይይት መድረኮችና መስክ ጉብኝቶች ላይ በመሳተፍ የራሱን ጉልህ ድርሻ እንደሚወጣ አክለው የጠቀሱት ክብርት ዋና ኦዲተሯ በተለይም አዲሱን የዲጂታል የግዥ ስርዓት በሁሉም ተቋማት ተግባራዊ በማድረግ በግዥ ሂደት የሚከሰቱ ብልሹ አሠራሮችን በመቅረፍ ግኝቶችን መቀነስ እንደሚገባና በይፋዊ ህዝባዊ ውይይቶችና የመስክ ምልከታ የሚመጡ የኦዲት ባለድርሻ አካላትም ከኦዲቱ አንጻር ከየተቋሞቻቸው የሚጠበቅባቸውን ግንዛቤ ይዘው ሊመጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ ዕቅዱ በሂደት እየታየና ተጨባጭ ሁኔታን ባደረገ መልኩ እየተከለሰ የሚሄድ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አክለውም እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል ለዕቅዱ መሳካት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣና በይፋዊ ህዝባዊ ውይይቶች ላይ የኦዲት ተደራጊ ተቋማት የበላይ አመራሮች እንዲገኙና በባለድርሻ አካላት ቅንጅት ለሚኒስቴር መ/ቤቶች ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ሊመቻቹ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡