News

መ/ቤቱ የትግራይ ክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤትን በቀጣይ በጀት ዓመት ወደ ሥራ ማስገባት የሚያስችል ሥልጠና ሰጠ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር  መ/ቤት የትግራይ ክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤትን በቀጣይ በጀት ዓመት ወደ ሥራ ማስገባት የሚያስችል ሥልጠና  መሰጠቱን  የመ/ቤቱ የትምህርትና ሥልጠና ዳሬክቶሬት አስታወቀ፡፡

የክልሉ ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከዚህ ቀደም በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ሥራ አቋርጦ የነበረና እና ሠራተኞቹም በስራ ላይ ያልነበሩ ሲሆን አሁን ላይ በተደረገው የሰላም ስምምነት እና መንግስት ክልሉን በተለያየ አግባብ እንዲደገፍ በሰጠው አቅጣጫ መሠረት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትም የክልሉን ዋና ኦዲተር መ/ቤት ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችል የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል፡፡

ከግንቦት 29 እስከ ሰኔ 03/ 2015 ዓ.ም በአክሱም ከተማ በተካሄደው ስልጠና 130 የፋይኔሺያል ኦዲተሮች በፋይኔሺያል ኦዲት ማንዋል /FAM/ እና በህጋዊነት ኦዲት ማንዋል /CAM/ ላይ እንዲሁም 50 የክዋኔ ኦዲተሮች በፈረንጆቹ በ2018 በተሻሻለው አዲሱ የክዋኔ ኦዲት ማንዋል ላይ ስልጠና መውሰዳቸውን የመ/ቤቱ  የትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጌትነት አለሙ ጠቅሰዋል፡፡

ሥልጠናው ተግባር ተኮር የሆነና ሰልጣኝ ኦዲተሮች ማግኘት የሚገባቸውን እውቀት እንዲጨብጡ ብሎም ወደ ሥራ ሲገቡ ለመተግበር በሚያስችላቸው አግባብ የተሰጠ መሆኑን አቶ ጌትነት አለሙ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም ሥልጠናው በፋይኔሺያል ኦዲት ማንዋል /FAM/ እና የህጋዊነት ኦዲት ማንዋል /CAM/ እንዲሁም በአዲሱ የክዋኔ ኦዲት ማንዋል አጠቃላይ አሠራርና እይታ ላይ ያተኮረ በመሆኑ ኦዲተሮቹን ቶሎ ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችልና ሥራቸውን  በጊዜ፣ በጥራት እና በብቃት ለማከናወን የሚያስችላቸው ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ሥልጠና አንድ ሳምንት ቀደም ብሎም በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ድጋፍ ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ በመጡ ሙያተኞች ለ5 ቀናት ለ223 የተቋሙ አጠቃላይ ሠራተኞች በስነ ልቡና ላይ ተኮረ የ “ማይንድ ሴት”ሥልጠና መሰጠቱ ታውቋል፡፡

ከወር በፊትም የትግራይ ክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትን መጎብኘታቸው እና ከፌዴራል ዋና ኦዲተር እና ም/ዋና ኦዲተር ጋር በነበራቸው ቆይታም መ/ቤቱ  ክልሉን ሊያግዝ በሚችልባቸው የአቅም ግንባታ፣ የግብዓትና የአሠራር ሥርዓቶች ዙሪያ መወያየታቸው ይታወሳል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *