የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ላይ በ2014 በጀት ዓመት ያካሄደውን የክዋኔ ኦዲት በሚመለከት በግኝቶቹ ላይ ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት አካሂዷል፡፡
መንገዱንና ሠራተኞችን ከአደጋ ከመጠበቅ፣ ከክብደት በላይ ጭነው በመንገዱ የሚጠቀሙ ተሸከርካሪዎችንና ፍጥነታቸውን ለመቆጣጠር የሚስያችል መመሪያና አሠራር አዘጋጅቶ ከመተግበር አንጻር ክፍተቶች መኖራቸውን ኦዲቱ እንደሚያሳይ ተነስቷል፡፡
ስለ መንገድና የመንገድ ሀብቶች ጥገና፣ በመንገዶቹ ላይ እየተገነቡ ስላሉ የአገልግሎት መስጫና የነዳጅ ማደያ ግንባታ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ በመንገድ መገልገያ ንብረቶች ስርቆት እና በግዥ አፈጻጸም ዙሪያ መሰረታዊ ችግሮች መኖራቸውም ተጠቁሟል፡፡
ተቋማዊ መዋቅርና ዕቅዶች የኢንተርፕራይዙን አገልግሎት የሚመጥኑ ያለመሆናቸውና ወጪን በመቆጠብ፣ ተጨማሪ የፋይናንስ ገቢ ለማስገኘት እየተሰሩ ባሉ ስራዎች እና በተሰብሳቢ ሂሳቦች ዙሪያም ሰፊ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡
የኢንተርፕራይዙ ዋና ስራ አስኪያጅ ክቡር አቶ ሙስጠፋ አባሰመልን ጨምሮ ሌሎች የተቋሙ አመራሮች በኦዲት ግኝቶቹ ዙሪያ ሰፊ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ከኦዲቱ በኋላ በርካታ የማሻሻያ እርምጃዎች መወሰዳቸውንና በዚህም ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡
የኦዲት ግኝቶቹ ትክክለኛና ሰፊ ስራ ለመስራት ያገዟቸው መሆኑን የጠቆሙት አመራሮቹ ቀሪ ግኝቶችን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተው ከተቋማቸው አቅም በላይ የሆኑና መንግስትን ጨምሮ የሌሎች ባለድርሻ አካላትን ድጋፍ የሚሹ ችግሮች እንዳሉባቸውም ጠቁመዋል፡፡
የኢንተርፕራይዙን ስራ ከመከታተልና ከመቆጣጠር ባለፈ ትርፉን የሚሰበስበው የኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አመራሮች በበኩላቸው የኢንተርፕራይዙ አመራር ቦርድ ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመው ችግሮችን በመለየት ሌሎች ድጋፎች ለማድረግ የሚያስችሉ የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጥረት እየተደረገ መሆኑንና ወደፊትም በተቋሙ ስራ ላይ ያላቸው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙ የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በኦዲት ግኝቶቹ ላይ አበረታች እርምጃዎች መወሰዳቸውንና ዝግጅት የተደረገበት ገላጭ ማብራሪያና ሪፖርት መቅረቡን አድንቀው ኢንተርፕራይዙ አፋጣኝ መፍትሔ ለሚሹ ቀሪ እርምጃዎች ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት ብለዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ በበኩላቸው ተቋሙ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ የድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅቶ ማቅረቡና ጥቂት በማይባሉ ግኝቶች ላይ የማስተካከያ እርምጃ መውሰዱ በበጎ መልኩ የሚታይ መሆኑን ጠቅሰው አሁንም ድረስ የመንገዶችን ደህንነት ከመጠበቅ አንጻር ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን በዝርዝር ጠቁመዋል፡፡
በመንገድ ላይ በቅለው በመንገድ አገልግሎት ላይ ችግር እየፈጠሩ ስላሉ አላስፈላጊ ተክሎች፣ ከክብደት በላይ ጭነው በመንገዱ ስለሚጠቀሙ ተሸከርካሪዎች፣ በመንገዱ በሚገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ መደረግ ስለሚገባው ቴክኒካዊ ፍተሻና የፍጥነት ቁጥጥር፣ ስለጥገና ዝርዝር ዕቅድ እና ተገቢ ስለሆነ ተቋማዊ መዋቅር፣ ስለ ተቋሙ የግንባታ ፕሮጀክቶች እና ሌሎች ግኝቶች አንስተው ተቋሙ በእነዚህ ግኝቶች ላይ ተገቢና አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው በግኝቶቹ ላይ የማሻሻያ እርምጃዎችን ለመውሰድ በተቋሙ በኩል እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታችና ለሌሎች ተቋማት ማስተማሪያ ነው ብለዋል፡፡
አክለውም መንገዱ የሀገሪቱን የመንገድ እድገት ከፍ ያደረገ ትልቅ ሀብት እንደመሆኑ ኢንተርፕራይዙ መንገዶቹን አለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መሰረት ባደረገ ስታንዳርድ ማስተዳደርና መምራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡
የመንገዶችን አገልግሎት የሚያውኩ አላስፈላጊ ነገሮችን ማስወገድ እና የመንገዱ አገልግሎት ሳይቆም ጥገናን ማከናወን እንደሚገባ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ አንስተው የጠቀሱት ክብርት ዋና ኦዲተሯ ችግሩን ለመፍታት የሌሎች አካላትን ውሳኔና ድጋፍ የሚጠይቅ ቢሆንም ከክብደታቸው በላይ በመንገዱ ስለሚገለገሉ ተሸከርካሪዎችና ሌሎች ክፍተቶች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡
በግዥ ስርዓት፣ በተጨማሪ የገቢ ማስገኛ መንገዶች፣ በፍጥነት መቆጣጠሪያ እና በተሰብሳቢ ገንዘቦች ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ማስወገድ እንደሚገባ በመጠቆምም የንብረት ስርቆትን ለማስወገድ በአጥፊዎቹ ላይ ተጠያቂነትን ማስፈንና ተቋማዊ መዋቅሩንም የኢንተርፕራይዙን ዓላማ የሚመጥን ማድረግ እንደሚያስፈልግም ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ም/ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ በበኩላቸው የኦዲት ግኝቶች ላይ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች በጠንካራ ጎኑ የሚታዩ መሆናቸውን ገልጸው ተቋሙ እንደ መንግስት የመንገድ እቅድ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው በመሆኑ ችግሮቹን በመቅረፍ ሀገሪቱ ወደፊትም ካላት ተመሳሳይ መንገዶች ግንባታ ዕቅድ አንጻር እራሱን ማዘጋጀትና ማዘመን ይገባዋል ብለዋል፡፡
አመራሩንና አሠራሩን በመፈተሸም በታዩ የኦዲት ግኝቶች ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ አሳስበው በተቋም ደረጃ የሚወሰዱ ቀሪ የማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰድና ከተቋም አቅም በላይ በሆኑት ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ግንኙነት በመፍጠር የተሻለ ስራ እንዲሰራና የኢንቨስትመንት ሆልዲንግስን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም የድርሻቸውን በመወጣት ለተቋሙ አስፈላጊ ድጋፎችን እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ተቋሙን ለመደገፍ አስፈላጊውን የክትትልና የድጋፍ ስራ እንደሚያከናውን ጨምረው በመግለጸም ተቋሙ ለቀጣይ የማሻሻያ እርምጃዎች የሚሆን የድርጊት መርሀ ግብር በአጭር ጊዜ ውስጥ አዘጋጅቶ ቋሚ ኮሚቴውን ጨምሮ ለሚመለከታቸው አካላት እንዲያቀርብና የአፈጻጸም ሪፖርቶችንም በየሁለት ወሩ እንዲልክ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡