የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የ2013 በጀት ዓመት የሂሳብ ህጋዊነት ኦዲት ግኝቶችን አስመልክቶ ይፋዊ የህዝብ ውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በዩኒቨርሲቲው የ2013 በጀት ዓመት የፋይንስ አሰራር እንዲሁም የንብረት አያያዝና አጠባበቅን በሚመለከት በካሄደው የሂሳብ ህጋዊነት ኦዲት መሰረት በርካታ የፋይናንስ አሠራር ክፍተቶችና የመመሪያ ጥሰቶች መታየታቸው በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡
ከብር 1.4 ሚሊዮን በላይ በጥሬ ገንዘብ ጉድለት መታየቱ፣ ከብር 1.1 ሚሊዮን በላይ በዱቤ ሽያጭ ደረሰኝ ክፍያ መፈጸሙ፣ ከብር 1 ሚሊዮን በላይ ከውስጥ ገቢ መከፈል የሚገባው የትርፍ ሰዓት ክፍያ ከመደበኛ በጀት ተከፍሎ መገኘቱ እና ከብር 83.8 ሚሊዮን በላይ ከ 1 ዓመት አስከ 5 ዓመት ያልተሰበሰበ ተሰብሳቢ ሂሳብ መኖሩ በመድረኩ ላይ ተነስቷል፡፡
በተጨማሪም ለባለመብቶቹ በወቅቱ ያልተከፈለ ከብር 4.6 ሚሊዮን በላይ ተከፋይ ሂሳብ መገኘቱ እና ሠራተኞች ከሚሰሩበት ስፍራ ሳይንቀሳቀሱ ከብር 3 ሚሊዮን በላይ በውሎ አበል ተመን ያላግባብ ክፍያ መፈጸሙ እንዲሁም ከብር 1.9 ሚሊዮን በላይ ለተከፈለ ክፍያ ተገቢ ህጋዊ ደረሰኝ ያለመቅረቡ እና ከብር 25.8 በላይ በሆነ ገንዘብ ከግዥ መመሪያ ውጭ የጄንሬተር ግዥ መፈጸሙ በመድረኩ ላይ ከተነሱ ጉልህ የፋይናንስ አሠራር ግድፈቶች መካከል ይገኛሉ፡፡
የንብረት አያያዝና አጠቃቀምን በተመለከተም በርካታ የንብረት አያያዝ ክፍቶቶች መታየታቸው የተጠቆመ ሲሆን ከ2008 እስከ 2011 በነበሩት በጀት ዓመታት በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተካሄዱና የማሻሻያ ሃሳብ ከተሰጠባቸው ኦዲቶች መካከል አሁንም ድረስ ጥቂት የማይባሉት የማሻሻያ እርምጃ ያልተወሰደባቸው መሆኑ ተነስቷል፡፡
በተነሱት የኦዲት ግኝቶች ላይ ምላሽ የሰጡት የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ግኝቶቹ ትክክለኛ መሆናቸውን ጠቁመው በርካታ ግኝቶች ከኦዲቱ በኋላ የማስተካከያ እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑንና በአጥፊዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን አንስተዋል፡፡ ግኝቶቹን ለማስተካከል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ስራዎች መሰራታቸውን የጠቆሙት ኃላፊዎቹ ተመላሽ ሂሳቦችን የማሰባሰብ ስራን ጨምሮ ቀሪዎቹንም ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
የተሰጡትን ምላሾች ተከትሎ አስተያየት የሰጡት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር የተከበሩ አቶ አበራ ታደሰ በበኩላቸው የተወሰኑ ግኝቶች ላይ የተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች አበረታች ቢሆኑም በርካታ ግኝቶች አሁንም ድረስ መፍትሔ ያልተሰጣቸው መሆኑን በዝርዝር አንስተዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የኦዲት ግኝቶችን ለማስተካከል እየወሰደ ያለው እርምጃ በበጎ የሚታይ ቢሆንም ከ2008 በጀት ዓመት ጀምሮ የታዩ የኦዲት ግኝቶች ላይ እርምጃ ሳይወሰድ መቅረቱ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ክፍተት ነው ብለዋል፡፡ ችግሮቹ የመንግስትን የአሠራር ደንብና መመሪያ ካለመከተል የመነጩና በተቋሙ ውስጥ ብልሹ አሰራር መኖሩን የሚጠቁሙ በመሆናቸው በክትትል ላይ የተመሰረተ የውስጥ ቁጥጥርን በማጠናከር አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው የኒቨርሲቲው በተወሰኑ ግኝቶች ላይ የወሰዳቸው የማሻሻያ እርምጃዎች የሚያበረታቱ መሆኑን ጠቁመው ከ2007 በጀት ዓመት ጀምሮ እየተንከባለሉ የመጡ የአሠራር ግድፈቶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ በ2013 በጀት ዓመት ከታዩት 16 ግኝቶች መካከል አስከ አሁን ድረስ በ6 ግኝቶች ላይ ብቻ የማስተካከያ እርምጃ መወሰዱን በማሳያነት የጠቆሙት ክብርት ዋና ኦዲተሯ ተገቢ ህጋዊ ደረሰኝ ካለማቅረብ፣ ከበጀት አጠቃቀም፣ ከተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳቦች፣ ህጋዊ ካልሆነ የአበል አከፋፈል ፣ከንብረት አያያዝና አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ችግሮች አሁንም ድረስ የቀጠሉ በመሆናቸው አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጣቸውና ከብልሹ አሰራር ጋር ግንኙነት ባላቸው አጥፊዎች ላይም አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የኦዲት ግኝቶቹን ለማስተካከል እያከናወነ ያለው ተግባር አበረታች መሆኑን ጠቁመው ግኝቶቹ የህዝብና የሀገርን ሀብት ላለተገባ ብክነት የሚዳርጉ መሆኑ ታውቆ አፋጣኝ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አሳስበዋል፡፡
ከግንዛቤ ማነስ፣ ከአሠራር ብልሹነትና መመሪያን ካለመከተል የመነጩት ክፍተቶች በቀላሉ የማይታዩ መሆናቸውን የጠቆሙት ም/ሰብሳቢዋ ተመላሽ ያልተደረጉ ሂሳቦች በአፋጣኝ ተመላሽ እንዲደረጉና የኒቨርሲቲውም ሆነ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ከትትል በማድረግ በግኝቶቹ ላይ ተገቢ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱ አሳስበዋል፡፡
አክለውም ዩኒቨርሲቲው የማሻሻያ የድርጊት መርሀ ግብሩን በመቅረጽ እስከ ሚያዚያ 20 ቀን 2015 ድረስ ለቋሚ ኮሚቴውና የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትን ጨምሮ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሪፖርት እንዲያደርግ እና የሚመለከታቸው ባለድርሻዎችም በክትትሉና እርምጃ አወሳሰዱ ላይ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አቅጣጫ በማስቀመጥ ቋሚ ኮሚቴውም የእርምጃ አወሳሰድ ሂደቱን በቅርበት ይከታተላል ብለዋል፡፡