የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የ2014/2015 በጀት ዓመት የሁለተኛ ሩብ አመት አፈጻጸሙን ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቀረበ፡፡
በመድረኩ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ አፈጻጸሙን አስመልክቶ ሰፊ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን መ/ቤቱ ዕቅዱን ካስቀመጣቸው ግቦች አንጻር ለማሳካት ያከናወናቸውን ተግባራት፣ በአፈጻጸሙ ያስመዘገባቸውን ውጤቶችና በእቅድ አፈጻጸም ወቅት የታዩ ጠንካራ ጎኖች እንዲሁም ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
የዋና ኦዲተሯን ገለጻ ተከትሎ የቋሚ ኮሚቴ አባላት አስተያየት የሰጡ ሲሆን ከቀረበላቸው ሪፖርት መ/ቤቱ አበራታች ስራዎችን እንደሰራ መገንዘባቸው ገልጸው ተጨማሪ ማብራሪያ በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡
የተነሱ ጥያቄዎችን መነሻ በማድረግ ክብርት ዋና ኦዲተር እና ም/ዋና ኦዲተሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በቋሚ ኮሚቴው የሚሰጡ አስተያየቶች ሁሌም ለተቋሙ ገንቢና አጋዥ መሆናቸውን ኃላፊዎቹ አስታውሰው ከዚህ የበለጠ መ/ቤቱ እንዲሰራ አሁንም የቋሚ ኮሚቴው እና የፓርላማው እገዛ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ም/ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ በበኩላቸው የቀረበው የዕቅድ አፈጻጸም አበረታችና ስኬታማ ሊባል የሚችል ነው ብለዋል፡፡
በተለይም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከቋሚ ኮሚቴው እና ከኦዲት ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ተናበው መስራታቸው በቀረበው የአፈጻጸም ሪፖርት ላይ አመርቂ ውጤቶች እንዲታዩ ማድረጉን ም/ሰብሳቢዋ ገልጸዋል፡፡
መ/ቤቱ ተቋማዊ አፈጻጸሙን የበለጠ በማጎልበት ባልተሟሉ የስራ መደቦች ቅጥር እንዲያከናውን እና የተሻለ የስራ አፈጻጸም ያሳዩ ሞዴል ሠራተኞችም የማበረታቻ ሽልማት የመስጠት ልምድ እንዲያዳብርና በትኩረት እንዲሰራ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ አሳስበው ቋሚ ኮሚቴውም መ/ቤቱ የተሻለ የስራ አፈጻጸም እንዲያስመዘግብ የሚያደርገውን ድጋፍ እና ክትትል አጠናሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
በመጨረሻም የመ/ቤቱ የሁለተኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸሙን እንዲጸድቅ ቋሚ ኮሚቴው በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡