በሲዳማ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ የተመራ የልዑክ ቡድን የፌዴራል ዋና ኦዲተር ቤትን የጎበኘ ሲሆን ከጉብኝቱ ሰፊና ጠቃሚ ተሞክሮዎችን እንዳገኘ ገልጿል፡፡
የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤና ም/አፈጉባኤ፣ የክልሉ ምክር ቤት የበጀት፣ ፋይናንስና ወጪ አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ እንዲሁም የክልሉ ዋና ኦዲተር እና ም/ዋና ኦዲተር በመገኘት ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ዋና ኦዲተር እና ምክትል ዋና ኦዲተር ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የህግ መሠረቶች፣ ተቋማዊ ነጻነት፣ የኦዲት አሠራር፣ ሪፖርት አቀራረብና እርምጃ አወሳሰድ፤ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ስላለው ግንኙነቶች እንዲሁም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለክልሉ ሊያደርጋቸው ስለሚችላቸው የድጋፍ አይነቶች ተዳሰዋል፡፡
የክልሉ አፈጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ፋንታዬ ከበደ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የተደረገላቸው ገለጻ በቂ ግንዛቤ የፈጠረላቸው እና በቀጣይ በክልላቸው መስራት ለሚፈልጉት ለውጥ ሰፊ ተሞክሮ የቀሰሙበት እንደሆነ ጠቁመው ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ክልሉ ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በዚህ ደረጃ ልምድ ለመቅሰም አስቦ በመምጣቱ ያላቸው አክብሮት ገልጸው በቀጣይ ክልሉን መ/ቤታቸው በሚችለው ሁሉ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከውይይቱ በኋላ የልዑክ ቡድኑ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የመረጃ ማዕከል /Datacenter/ ጎብኝቷል፡፡