የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት ስርዓት አፈፃፀምን በተመለከተ በ2013/14 በጀት ዓመት ባካሄደው የክዋኔ ኦዲት መሰረት ለቅመማ ቅመም ምርት አስፈላጊው ትኩረት አልተሰጠም ተባለ፡፡
በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥር 17 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት እንደተገለጸው ለቅመማ ቅመም ግብይትና ጥራት ቁጥጥር የተዘጋጀው መመሪያ ያለመጽደ እና የቅመማ ቅመም ልማትና ኤክስቴንሽን የማስተዋወቅና የማስፋፋት ስራዎች ባለመሰራታቸውም ሀገሪቱ ከቅመማ ቅመም ምርት ማግኘት የሚገባትን ገቢ ማግኘት እንዳልቻለች በመድረኩ ላይ ተጠቅሷል፡፡
የቅመማ ቅመመ ምርት ጥራትና ጣዕም ምርመራ ማዕከላት አለመቋቋማቸው እና የጥራት ማረጋገጫ ሰርተፊኬሽን ማዕከላት በዘመናዊ ላቦራቶሪዎች ተደግፈው አለመቋቋማቸው ፣ በባለስልጣን መ/ቤቱ የገበያ ማስፋፊያና ትስስር ተጠናክሮ አለመሰራቱ እና ወደ ዓለም ገበያ የሚያስገባና ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችል ስልት አለመነደፉ እንዲሁም የኤክስፖርት ስትራቴጂ አለመዘጋጀቱ በኦዲት ግኝቱ ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም ለአርሶ አደሩ ማሰልጠኛዎችና ሰርቶ ማሳያ ቦታዎች አለመደራጀታቸው እና በቅመማ ቅመም ምርቶች ላይ እሴት ለመጨመር የሚያስችል ሀገራዊ አቅም ለመገንባት ከመሚመለከታቸው አካላት ጋር በተቀናጀ መልኩ አለመሰራቱ በኦዲቱ ወቅት መረጋገጡ ተነስቷል፡፡
የባለስልጣን መ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ደበላ በተነሱት የኦዲት ግኝቶች እና ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በማብራሪያቸውም ባለስልጣን መ/ቤቱ ለቅመማ ቅመም ግብይትና ጥራት ቁጥጥር መመሪያ መዘጋጀቱንና በተያዘው በጀት ዓመት 3ኛው ሩብ ላይ እንደሚጸድቅ ጠቁመው የቅመማ ቅመም ልማትና ኤክስቴንሽንን የማስተዋወቅና የማስፋፋት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ወደ ዓለም ገበያ እንዲገቡና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ 16 ዋና ዋና ቅመሞች መለየታቸውን እና የኤክስፖርት ስትራቴጂም መዘጋጀቱን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ በአጠቃላይ ለባለሙያዎችና ለአርሶ አደሮች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙ የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች የኦዲት ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው ባለስልጣን መ/ቤቱ የኦዲት ግኝቶቹን መሰረት ያደረገ የማስተካከያ እርምጃ ያልወሰደ መሆኑን ከተሰጠው ግብረመልስ ለመረዳት መቻሉን ጠቅሰው ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት በሚገባት ገቢ ማስገኛ ዘርፍ ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ክብርት ዶ/ር ሶፍያ ካሳ በበኩላቸው በኦዲት ግኝት የተገኙት እና በመድረኩ የተሰጡ አስተያየቶች በአዎንታዊ መልኩ እንደሚቀበሉት ጠቅሰው ባለስልጣን መ/ቤቱ የሚኒስቴር መ/ቤቱ ተጠሪ እንደመሆኑ በግኝቶቹ ላይ ተገቢውን ክትትል በማድረግ ችግሮቹን ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
የክዋኔ ኦዲት ለማድረግ ሲታሰብ በሀገሪቱ ያለውን የቅመማ ቅመም ምርት አቅም በመረዳትና ከፍተኛ ሀገራዊ ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑንም በማሰብ መሆኑን በማብራሪያቸው የጠቀሱት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው ወደ ምርት ከመገባቱ በፊት ቅድሚያ መዘጋጀት ያለበት አዋጅ፣ የአሠራር ደንብ እና መመሪያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ባለስልጣን መ/ቤቱ ምርታማነትን ለማሳደግ ስትራቴጂዎች መንደፍ እንደሚገባው ጨምረው የገለጹት ክብርት ዋና ኦዲተሯ የቅመማቅመም ሰብልን ከሚያጠቃ በሽታ ለመከላከል የሚያስችል ትኩረት እንደሚያስፈለግና የምርት ጥራቱን በመጠበቅና የሰርተፊኬሽን ስርዓቱን በማጠናከር በዘርፉ ላይ አጠቃላይ እሴት መጨመር እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡
የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስትያን ታደለ በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ በመድረኩ ላይ በባለስልጣን መ/ቤቱ የተሰጠው ምላሽ አጥጋቢ ባይሆንም የተሰጡ የማሻሻያ ሀሳቦችን ለመቀበል እና ግኝቶችን ለማስተካከል የታየው ተነሳሽነት አበረታች ነው ብለዋል፡፡
ባለስልጣን መ/ቤቱ የተሰጡትን አስተያየቶች መሰረት በማድረግ እና የማሻሻያ እርምጃ በመውሰድ እስከ ጥር 27 ቀን 2015 ድረስ ሪፖርት እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ እርምጃዎች የተቋማት አፈጻጸምና የአመራር ሰጪነት ብቃት መመዘኛ መሆን እንደሚገባቸውና ይህ ተግባራዊ ስለመሆኑም የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ማረጋገጫ ሪፖርት እንዲያቀርብ ጨምረው ያሳሰቡት የተከበሩ አቶ ክርስትያን ግብርና ሚኒስቴርም ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ እንዲያደርግና የቋሚ ኮሚቴ አባላት እና የሚመለከታቸው የኦዲት ባለድርሻ አካላትም አስፈላጊውን ተጨባጭ ክትትልና ድጋፍ አንዲያደርጉ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
ለተጨማሪ ግንዛቤ የሚከተለውን ሊንክ ይጫኑ፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=veF4keilAbg