News

ከመንግስት የአሠራር ደንብና መመሪያ ውጪ መስራት ህገ ወጥነት መሆኑ ተገለጸ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የስቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን  የ2013 በጀት ዓመት የሂሳብ ሪፖርቶችንና ማስታወሻዎችን መሠረት በማድረግ ባካሄደው የሂሳብ ህጋዊነት ኦዲት መሰረት የአሠራር ደንብና መመሪያን የጣሱ የፋይናንሽያል ሥርዓት እና የሂሳብ አያያዝ ችግሮች መታየታቸው ተጠቆመ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አማካይነት ጥር 17 ቀን 2015 ዓ.ም በተካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ የውይይት መድረክ እንደተገለጸው በገቢና ወጪ ሂሳቦች፣ በተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳቦች እንዲሁም በንብረት አያያዝና አወጋገድ ስርዓት ላይ ጉልህ ክፍተቶች ታይተዋል፡፡

የገቢ ሂሳብን በተመለከተ ብር 4,110,339.91 በዴቢት እንዲሁም ብር 10,824,783.36 በክሬዲት ለተመዘገቡ ሂሳቦች በኦዲት ወቅት ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ የሂሳቡን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ያለመቻሉ፣ በኦዲቱ ወቅት ደጋፊ የጨረታ ሰነድ ባለመቅረቡ የገቢውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ያልተቻለ ብር 1,676,679.00 መገኘቱ እና  በመንግስት ደንብና መመሪያ መሠረት ወደ ኤጀንሲው የባንክ ሂሳብ ወይም ማዕከላዊ ግምጃ ቤት በየዕለቱ ገቢ መደረግ የነበረበት በጥቅሉ ብር 338,358.30 በየዕለቱ ገቢ ሳይደረግ መገኘቱ  በመድረኩ ላይ ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም  በኦዲቱ ወቅት ተገቢ የሰነድ ማስረጃ ያልቀረበበት 19,651,132.67 በወጪ ሂሳብ መደብ ተመዝግቦ መገኘቱ፣ የጸደቀ ደንብ ሳይኖር በማኔጅመንት ኮሚቴ ውሳኔ ብቻ ብር 153,141.66 ለሠራተኞች የትራንስፖርት አበል ተከፍሎ መገኘቱ፣ የኤጀንሲው የስራ ኃላፊዎች ለሀገር ውስጥ ህክምና የተጠቀሙበት ብር 3,755.16 ተቀንሶ ለሚመለከተው አካል ገቢ ያለመደረጉ፣ ተሰብሳቢ ሂሳብን በተመለከተ ብር 35,017.50 ከአምስት አመት በላይ ለሆነ ጊዜ ያልተሰበሰበ መሆኑ እና ተከፋይ ሂሳብን በተመለከተም በድምሩ 18,698,927.85 ከ10 ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ ለሚመለከተው አካል ሳይከፈል መቆየቱ  በኦዲቱ መረጋገጡ ተነስቷል፡፡

ከዚህም ሌላ ህጋዊ በሆነ አግባብ መወገድ የሚገባቸው በርካታ የተሸከርካሪ እና የቢሮ መገልገያ እቃዎች በመጋዘን ውስጥ ተከማችተው መገኘታቸው በኦዲቱ ወቅት መታየቱ ተገልጿል፡፡ እነዚህ ችግሮች ለምን እንደተከሰቱና ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተሰጡ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ አስተያየቶች መሰረት ችግሮቹን ለመቅረፍ ምን  እርምጃ እንደተወሰደም ከመድረኩ ተጠይቋል፡፡

የባልስልጣን መ/ቤቱን  ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦን ጨምሮ በመድረኩ የተገኙት የኤጀንሲው አመራሮች በተነሱት የኦዲት ግኝቶች እና ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያና ምላሽ የሰጡ ሲሆን ባለስልጣን መ/ቤቱ ከለውጡ በኋላ ቀደም ሲል በመንግስትና በሲቪል ማህበራት ድርጅቶች መካከል የነበረውን አሉታዊ ግንኙነት አዎንታዊ ለማድረግና አሠራሮቹን ለማሻሻል በርካታ የሪፎርም ስራዎችን መስራቱንና በዚህም ስኬታማ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡

የተጠቀሱት የኦዲት ግኝቶች ትክክለኛ መሆናቸውን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ ችግሮቹ በቦታው ላይ ከነበሩት ባለሙያዎች የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አቅም ማነስ እንዲሁም በአሠራር መዛባትና በሂሳብ አመዘጋገብ ክፍተት የተከሰቱ መሆናቸውን ጠቅሰው ችግሮቹን ለመቅረፍ የማሻሻያ እርምጃዎች ተወስደዋል ብለዋል፡፡ አክለውም የኦዲት ግኝቶቹን ለማስተካከል በተወሰደ እርምጃ ከፊሎቹን ግኝቶች ማስተካከል መቻሉንና ቀሪዎችንም ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ በባለስልጣን መ/ቤቱ አመራሮች የተሰጡ ምላሾችን ተከትሎ በሰጡት አስተያየት በአጠቃላይ የኦዲት ግኝቶቹ አስር ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል ሶስቱ ግኝቶች ከኦዲቱ በኋላ በተሰጠው የኦዲት ግኝት ማሻሻያ መሰረት  እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ ከግኝቶቹ መካከል ሁለቱ በከፊል እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑን ጨምረው የጠቀሱት ም/ዋና ኦዲተሩ ቀሪዎቹ አምስት ግኝቶች አስከአሁን ድረስ ሙሉ ለሙሉ እርምጃ ያልተወሰደባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙ የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች የኦዲት ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው ባለስልጣን መ/ቤቱ የኦዲት ግኝቶቹን ተከትሎ የወሰዳቸው እርምጃዎች በበጎ መልኩ የሚታዩ መሆናቸውን በመጥቀስ በቀሪዎቹ ግኝቶች ላይ አፋጣኝ እርምጃ መወስድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡  ግኝቶቹ የአሠራር ደንብና መመሪያን ካለመከተል፣ ከአሠራር አቅም ማነስ፣ የሂሳብ ሰነዶችን በአግባቡ አደራጅቶ ካለመያዝ፣ ለዘመናዊ አሠራርና ለሂሳብ አመዘጋገብ ትኩረት ካለመስጠት የተከሰቱ በመሆናቸው እነዚህን ጉልህ የአሠራር ክፍተቶች ማረምና ከተለመደው አሠራር በመውጣት ወቅቱ የሚጠይቀውን ዘመናዊ አሠራር እንዲሁም ተገቢ ደንብና መመሪያን መተግበር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡ ተቋሙ በርካታ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን የሚመራና የሚቆጣጠር መሆኑን ጨምረው የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ ለእነዚህ ድርጅቶች ሞዴል ሆኖ መቅረብ ይገባዋል ብለዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የፍትሕ ሚኒስትሩ ክቡር ዶ.ር ጌዴዮን ጢሞቲዎስ በበኩላቸው አሠራሮችን ከተለምዶው አሠራር ወደ ዘመናዊ አሠራር ለመቀየር በቦታው ላይ የሚገኙ ባለሙያዎችን ማብቃት አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ  ባለስልጣን መ/ቤቱ ለሚኒስቴር መ/ቤታቸው ተጠሪ እንደመሆኑ በተዘጋጀው የድርጊት መርሀ ግብር መሰረት በግኝቶቹ ላይ ትኩረት ያለው ክትትል በማድረግ ግኝቶቹን ለማስተካከል አስፈላጊው ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ የኦዲት ግኝቶቹን፣ ከባለስልጣን መ/ቤቱ የተሰጡ ምላሾችንና  ከመድረኩ የተነሱ ነጥቦችን መሰረት በማድረግ በሰጡት አስተያየት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የኦዲት ግኝቶቹን ተከትሎ የወሰዳቸው  የኦዲት ግኝት ማሻሻያ እርምጃዎች የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል፡፡ ከግኝቶቹ መካከል ጥቂት የማይባሉ ግኝቶች አሁንም ድረስ  የኦዲት ማሻሻያ እርምጃ ያልተወሰደባቸው መሆኑን የጠቀሱት ክብርት ዋና ኦዲተሯ በተለይም በኦዲት ወቅት አስፈላጊ የሆኑ የሰነድ ማስረጃዎችን ያለማቅረብ  የተቋሙ ችግር አሁንም ድረስ መታረም ያልቻለ ነው ብለዋል፡፡

ከፊሎቹ ማስተካከያ የተወሰደባቸው ቢሆኑም በኦዲቱ ወቅት በጥቅሉ ገቢን በተመለከተ  ለብር 10.8 ሚሊዮን እንዲሁም ወጪን በተመለከተ ለብር 19.6 ሚሊዮን  ተገቢ የሰነድ ማስረጃ ያልቀረበ መሆኑን ያስታወሱት ክብርት ወ/ሮ መሠረት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የ2013 በጀት ዓመት ሪፖርቱን ሲያቀርብ ባለስልጣን መ/ቤቱ የኦዲት አስተያየት መስጠት ካልተቻለባቸው ተቋማት መካከል የነበረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አክለውም በተለይም የመንግስት ደንብና መመሪያን ያለመከተል እና የሰነድ ማስረጃዎችን ለኦዲተሮች ያለማቅረብ ችግሮች በፍጥነት እንዲታረሙና የፍትሕ ሚኒስቴርም ለእነዚህ ችግሮች ህጋዊ መፍትሔ በመስጠት የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም የማጠቃለያ ሀሳብ የሰጡት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስትያን ታደለ በበኩላቸው ባለስልጣን መ/ቤቱ የኦዲት ግኝቶችን ለማሻሻል እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን በመጥቀስ እርምጃ ያልተወሰደባቸው ግኝቶች ላይ ትኩረት በመስጠት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የሰድ ማስረጃዎችን ለኦዲተሮች ለማቅረብ ፍላጎት ያለማሳየት ፣ ከህግና መመሪያ ውጪ አበል የመክፈል እንዲሁም በንብረት አያያዝና አጠቃቀም ረገድ የታዩ ችግሮች  አሁንም ድረስ የቀጠሉ በመሆኑ እነዚህ የህግና መመሪያ ጥሰቶች በፍጥነት መታረም ያለባቸው መሆኑን የጠቀሱት ሰብሳቢው ባለስልጣን መ/ቤቱ የበርካታ ሲቪል ድርጅቶች ተቆጣጣሪና መሪ እንደመሆኑ  ምሳሌ የሚሆን አሠራር ሊኖረው ይገባል ብለዋል፡፡ የመንግስት ህግና መመሪያን  በመጣስ ተቋሙ በህግ ከተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት ውጪ የሰራቸው ስራዎች ተቀባይነት የሌላቸው በመሆኑ በፍጥነት መታረም ያለባቸው መሆኑን በአጽንኦት ያሳሰቡት የተከበሩ አቶ ክርስትያን የፍትሕ ሚኒስቴርና ገንዘብ ሚኒስቴር የባለስልጣን መ/ቤቱን ችግሮች ለመቅረፍ ተገቢ ስራ መስራት አለባቸው ብለዋል፡፡

አክለውም ባለስልጣን መ/ቤቱ የተሰጡትን  አስተያየቶች መሰረት በማድረግ በግኝቶች ላይ የማሻሻያ እርምጃ በመውሰድ የድርጊት መርሀ ግብሩንና የተሠሩ ስራዎችን እስከ ጥር 27 ቀን 2015 ድረስ በሪፖርት እንዲያቀርብና ተከታታይ የአፈጻጸም ሪፖርቶችንም በየሶስት ወሩ እንዲያቀርብ እንዲሁም ተመላሽ መሆን የሚገባው የመንግስት ገንዘብ ተመላሽ እንዲደረግና መመሪያን በጣሱ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ ተገቢ አስተዳደራዊ  እርምጃ ተወስዶ ሪፖርት እንዲደረግ  ያሳሰቡ  ሲሆን የሚመለከታቸው የቋሚ ኮሚቴ እና ባለድርሻ አካለትም በባለስልጣን መ/ቤቱ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ እርምጃዎች አወሳሰድ ላይ  አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ሪፖርት እንዲያቀርቡ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

የሚከተለውን ሊንክ በመጫን የውይይት መድረኩን ሙሉ ሂደት መከታተል ይችላሉ፡፡

https://www.youtube.com/watch?v=ycE8GMJsNNg

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *