የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር ከተሸከርካሪዎች የሚለቀቁ የሙቀት አማቂ ጋዞች ልኬትና ቁጥጥር ሥርዓት አፈጻጸም በተመለከተ በ2013/2014 በጀት ዓመት ያካሄደውን የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት መነሻ በማድረግ በርካታ ክፍተቶች መታየታቸው ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥር 8 ቀን 2015 ባካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት ላይ ነው፡፡
በመድረኩ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከተሸከርካሪዎች የሚወጡ ሙቀት አማቂ ጋዞችን ለመቀነስ የተዘጋጁ ስትራቴጂዎች ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያላሳተፉ መሆናቸውንና ስታንዳርዱ ወጥቶ ተግባራዊ ያለመደረጉን፤ ከተሸከርካሪዎች የሚለቀቀውን የሙቀት አማቂ ጋዝ መጠን ለመቀነስ በዕቅድ ተይዞ ተግባራዊ ያለማድረጉን እና በሚኒስቴር መ/ቤቱ፣ በፌዴራል እና በክልል ባለድርሻ አካላት የሙቀት አማቂ ጋዞች መጠን ለመለካት የሚያስችል ዘመናዊ መሣሪያ እንዲኖር ያለማድረጉ ተነስቷል፡፡
በተጨማሪም ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከተሸከርካሪዎች የሚወጡ ሙቀት አማቂ ጋዞች ያሉበትን ደረጃ በማጥናት የጥናት ውጤቱን ተግባራዊ አለማድረጉን፣ ከክልል የትራንስፖርት ቢሮዎች ጋር በመሆን ጠንካራና ቀጣይነት ያለው መደበኛ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓት ያለመዘርጋቱን፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የሙቀት አማቂ ጋዞችን ለመቀነስ የሚያስችሉ ለትራንስፖርት አገልግሎት የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን ያለሟሟላቱም ተገልጿል፡፡
እንዲሁም ሚኒስቴር መ/ቤቱ ብዙ ዘመን ያገለገሉና ያረጁ ተሽከርካሪዎችን ከአገልግሎት/ከመንገድ የሚወጡበትን የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ሲገባው ተግባራዊ ያለማድረጉን እንዲሁም የሙቀት አማቂ ጋዞች ልኬትና ቁጥጥር ተግባራዊ ለማድረግ የተጠያቂነት ሥርዓት ያለመዘርጋቱ በመድረኩ የተነሱ ዋና ዋናዎቹ የኦዲት ግኝቶች ናቸው፡፡
በመድረኩ የተነሱትን የኦዲት ግኝቶች መሠረት በማድረግ በውይይቱ የተገኙት የትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በርኦ ሀሰንን ጨምሮ ምላሽ የሰጡት የሚኒስቴር መ/ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች የኦዲት ግኝቶቹ ተገቢና ትክክለኛ መሆናቸውን ጠቅሰው ከኦዲቱ በኋላ የወሰዷቸውን የማሻሻያ እርምጃዎች አብራርተዋል፡፡
በማብራሪያቸው የሙቀት አማቂ ጋዞችን ለመቀነስ የሚያስችል አዲስ ስታንዳርድ መዘጋጀቱን፣ እና በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሸከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ በስፋት እንዲገቡ ለዚህም ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ከክልልና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ከመስራት አኳያም ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን፣ ለረጅም ዓመት ያገለገሉ መኪኖች ከመንገድ ለማውጣት የሚያስችል ስታንዳርድ ያዘጋጁ ቢሆንም በተሸከርካሪዎቹ ጥገኛ የሆነውን የህብረተሰብ ክፍል ሳይጎዳ ከአገልግሎት የሚወጡበትን አማራጭ መፍትሔ እያጤኑ መሆኑን የሥራ ኃፊዎቹ አስረድተዋል፡፡
የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትና ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው ከተሸካሪዎች የሚለቀቁ የሙቀት አማቂ ጋዞች ልኬትና ቁጥጥር ሥርዓት አፈጻጸም ላይ ስፋት ያላቸው ችግሮች ያሉ በመሆኑ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከሚመለከታው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ የኦዲት ተደራጊ መ/ቤት የሥራ ኃላፊዎችን ምላሽ ተከትለው የተለያዩ አስተያየትና ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡
በአስተያየታቸው ሚኒስቴር መ/ቤቱ የድርጊት መርሃ ግብር በወቅቱ አዘጋጅቶ ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት መላኩ እና የ10 ዓመት ዕቅድ ውስጥ ስለሞተር አልባ ትራንስፖርት፣ ብዙሃን ትራንስፖርት እና የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች አካቶ እየሠራ መሆኑ በጥንካሬ አንስተው አሁንም ባልተሠሩ በርካታ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡
በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የብስክሌት አገልግሎት እንዲሰጡ የተዘጋጁ 3 መንገዶች አገልግሎት መቋረጣቸውን፣ በረቂቅ ደረጃ ተዘጋጅተው የነበሩ የመንገድ ትራንስፖርት ፖሊሲ፣ የብዙሃን ትራንስፖርት ፖሊሲና የአውቶሞቲቭ ስትራቴጂ የባለድርሻ አካላት ምክክር ያላደረጉበትና ያላጸደቁት መሆኑን፤ የትራንስፖርት ህጎች በሀገር አቀፍ ከወጡ የአከባቢ ህጎች ጋር እንዲጣጣሙ ያለመደረጉን እና የሙቀት አማቂ ጋዞች ያሉበት ደረጃ አለመጠናቱን አንስተው ሚኒስቴር መ/ቤቱ በኦዲቱ ምክረሃሳቦች መሰረት እየወሳደቸው ስላሉ የማሻሻያ እርምጃዎች ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ኦዲቱ 2 የትኩረት አቅጣጫዎችን መሠረት በማድረግ ወደ ሥራ መገባቱን አስታውሰው ከአሠራር ሥርዓት መዘርጋት አኳያ ስታንዳርድ በወቅቱ አለመዘጋጀቱን እና የሙቀት አማቂ ጋዞች መቆጣጠሪያ መሣሪያ ተገዝቶ አገልግሎት ላይ እንዲውል እስከአሁን አለመደረጉን አንስተዋል፡፡ ይህንንም ለመቅረፍ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ለተግባራዊነቱ ጠንከር ያለ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡
አያይዘውም ሚኒስቴር መ/ቤቱ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን አገልግሎት ማስፋት እንደለበት፣ ያገለገሉ መኪኖችን ከውጭ የማይገቡበት አግባብ ላይ ይበልጥ ጥኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ፣ የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚነትን ለማስፋት ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚሄዱ ጥናቶችን ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ዋና ኦዲተሯ አንስተዋል፡፡
የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በክልልም ሆነ በአዲስ አበባ የጀመራቸውን በጎ ጅምሮች አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠቁመው ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
አያይዘውም ሚኒስቴር መ/ቤቱ በጤና ሚኒስቴር ከተቀመጡ ከአንድ እስከ አስር የጤና ችግር አምጪ መንስኤዎች አንዱ ከተሸከርካሪዎች የሚወጡ የሙቀት አማቂ ጋዞች በመሆናቸው የተጠናከረ የቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት መፍትሔ ሊያበጅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡