News

ለክልል እና ለከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች የሚደረገው የአቅም ግንባታ ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል

የፌዴራል ዋና ኦዲተር /ፌዋኦ/ መ/ቤት ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤት ኦዲተሮች እና የሥራ ኃላፊዎች በፋይኔሺያል የኦዲት ማንዋል ላይ ሥልጠና ሰጠ፡፡

ስልጠናው በዋናነት የከተማ መስተዳድሩ ዋና ኦዲተር መ/ቤት እስከአሁን ይጠቀምበት የነበረውን የRAM (Regularity Audit Manual) ሥርዓት ወደ FAM (Financial audit Manual) የሚቀይረው መሆኑን በፌዋኦ የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት በተገኘ መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር ወ/ሮ ፈኪያ መሐመድ ስልጠናው አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለከተማ አስተዳደሩ ዋና ኦዲተር መ/ቤት ትኩረት በመስጠት የአቅም ግንባታ ድጋፍ በመደረጉ አመስግነው ድጋፍና ትብብሩ በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አሁን ያገኙት ሥልጠናም መ/ቤቱ ሲጠቀምበት የነበረውን ነባር የኦዲት ማንዋል በአዲሱ የኦዲት ማንዋል እንዲያሻሽሉ እንደሚያስችላቸው የገለጹት ዋና ኦዲተሯ ቀጣይ ሥራቸውንም ዘመናዊና ቀላል እንደሚያደርግላቸው ተናግረዋል፡፡

ሰልጣኝ ኦዲተሮች በበኩላቸው ሥልጠናው የተሰጠበት መንገድ ተግባር ተኮር በመሆኑ ማግኘት የሚገባቸውን እውቀት በቀላሉ እንደጨበጡ እንዳስቻላቸውና ለመተግበርም እንደማይቸገሩ ገልጸዋል፡፡

አዲሱ የኦዲት ማንዋልም ስራን በጊዜ፣ በጥራት እና በብቃት ለማከናወን ከማስቻሉም በላይ የኦዲት ሂደቱን የሚያቀልና የበለጠ ውጤታማ የሚያደርግ መሆኑንም ተገልጿል፡፡

ስልጠናው በሐረር ከተማ ከህዳር 26 እስከ ህዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም ለ5 ተከታታይ ቀናት የተሰጠ ሲሆን በስልጠናውም ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤት 46 ኦዲተሮች እና የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *